” በእግርኳስ ህይወቴ ብዙ የማሳካቸው ነገሮች ስለሚኖሩ በሚሰጡኝ አድናቆቶች አልዘናጋም ” አቡበከር ነስሩ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ትላንት ኢትዮጵያ ቡና ወደ ሀዋሳ ተጉዞ በሲዳማ ቡና ሽንፈት ቢያስተናግድም ታዳጊው አቡበከር ነስሩ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን አድርጎ ጎል አስቆጥሯል፡፡ ከወደፊቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ተስፋዎች አንዱ የሆነው አቡበከር ከጨዋታው በኋላ በእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

አጀማመር እና ያሳየው እድገት

እግር ኳስን የጀመርኩት ሰፈር ውስጥ በመጫወት ነው። በማደርገው እንቅስቃሴ የተደሰተው ፈለቀ የሚባል ሰው ኒያላ ታዳጊ ቡድን እንድመሞክር አድርጎኝ ቃሊቲ እየሄድኩ መጫወት ጀመርኩ፡፡ ነገር ግን ብዙም አልቆየሁም፡፡ ከቤቴ ወደ ቃሊቲ ሩቅ  ስለነበር ነው አቆምኩ፡፡ በመቀጠል የሐረር ሲቲ ምክትል አሰልጣኝ የሆነው ደግፌ ሐረር ሲቲ እንድጫወት አደረገኝ፡፡ እዛም ቡድን ተቀላቅዬ መጫወት ጀመርኩ ጥሩ ስልጠናና ልምድ በማግኘቴ በቡድኑ ውስጥ መጫወት ቻልኩ፡፡ ይሄም ለኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን እንድመረጥ አደረገኝ፡፡ በመቀጠል በዘንድሮ አመት ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቀልኩ።

የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን

በሐረር ሲቲ በነበረኝ ቆይታ ጥሪው ቀርቦልኝ ስሄድ አስቤ የነበረው 18 ውስጥ መግባትን ነበር። ሆኖም ቋሚ የመሆን አጋጣሚ አግኝቼ ከግብፅ እና ከማሊ ጋር በደርሶ መልስ አራት ጨዋታ አድርጌ ግብፅ ላይ ሁለት ጎል አስቆጥሬያለሁ። በነበረኝ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ቆይታ በአይምሮም በአካል ብቃትም በስልጠናም ጥሩ ነገር አግኝቻለው ።

ኢትዮዽያ ቡናን የተቀላቀለበት መንገድ

ኢትዮዽያ ቡና የልጅነት ህልሜ ነው፡፡ ለቡና መጫወትን አስብ ነበር። የቡናም ደጋፊ ነበርኩ፡፡ ካታንጋ እየገባውም ከሰፈር ልጆች ጋር እመለከት ነበር። ዘንድሮ የ17 አመት በታች ቡድን አሰልጣኙ ታዲዮስ ነው ወደ ቡና እንድገባ ያመጣኝ፡፡ ከሐረር ሲቲ ወደ ቡና ከመዘዋወሬ ጋር ተያይዞ ክርክሮች ነበሩ። ችግሩ በውይይት ተፈትቶ ነው ልገባ የቻልኩት፡፡ ምንም እንኳ ከመስከረም ወር ጀምሮ ካምፕ ገብቼ ከዋናው ቡድን ጋር ብሰራም የመጫወት ፍቃድ ያገኘሁት እና የፈረምኩት መጋቢት ወር መጀመርያ ላይ ነው።

በመጀመርያ የሊግ ጨዋታው ግብ ማስቆጠር

ጨዋታው የፕሪሚየር ሊግ ነው፡፡ በዛ ላይ ኢትዮዽያ ቡና ትልቅ ቡድን ነው፡፡ ጨዋታው በጣም ነበር የሚከብደው፡፡ ያው ጥሩ ባልንቀሳቀስም የመጀመርያ የፕሪሚየር ሊግ ጎሌን በማስቆጠሬ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ከፈጣሪ ጋር ጠንክሬ በመስራት ኢትዮዽያ ቡናን ማገልገል እፈልጋለው።

ከወዲሁ ሙገሳና አድናቆት መበርከቱ በወደፊት ህይወቱ ላይ የሚፈጥረው ጫና

በጣም ነው የምጠነቀቀው፡፡ እነ መስኡድ መሀመድን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ምን ማድረግ እንዳሉበኝ ይመክሩኛል፡፡ ስለዚህ እኔ የምፈልገው ማደግ ነው፡፡ ገና የመጀመርያ ጨዋታዬ ነው፡፡ ገና ብዙ ይቀረኛል፡፡ ወደ ፊት ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ረጅም ጉዞ መጓዝ እፈለጋለሁ፡፡ በዋናው ብሔራዊ ቡድንም መጫወት እመኛለው፡፡ ከኢትዮዽያ ውጭ ወጥቶ መጫወት ፍላጎቱ ስላለኝ አድናቆቱ አያዘናጋኝም፡፡

አሁን ለደረሰበት የእግር ኳስ ህይወት የሚያመሰግናቸው ግለሰቦች

በመጀመርያ እናትና አባቴን ማመስገን እፈልጋለው፡፡ ከዛም የሰፈሬ ሰዎች ኳስ እንድጫወት ያበረታቱኝ ነበር ፤ እነሱንም አመሰግናለው። በመቀጠል በእኔ እግር ኳስ ህይወት የማልዘነጋው ምርጥ አሰልጣኝ የሆነው እስማኤል አቡበከር ትልቁን ድርሻ ይወስዳልና እርሱን ማመስገን እፈልጋለው፡፡

1 Comment

Leave a Reply