የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ከተጀመረ አንድ ወር አስቆጥሯል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም በወሩ የተደረጉ ጨዋታዎች ላይ በግላቸው ምርጥ አቋም ያሳዩ ተጫዋቾችን እንደተለመደው ወሩን ጠብቃ የየካቲት መጋቢት ወር ምርጦችን ይፋ አድርጋለች፡፡

ማስታወሻ

* የተመረጡት ተጫዋቾች የወሩ አቋማቸውን ብቻ ግንዛቤ ውስጥ የከተተ ነው፡፡

ግብ ጠባቂ

ለአለም ብርሀኑ ( ሲዳማ ቡና )

የሊጉ መሪ የሆነው ሲዳማ ቡና ግብ ጠባቂ እና አምበል የሆነው ለአለም ለቡድኑ የዚህ ወር ድንቅ አቋም ዋነኛ ተጠቃሽ ተጨዋቾች መሀል አንዱ ነው። ከ15ኛው ሳምንት ጀምሮ በተደረጉ ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት ለአለም በርካታ ግብ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ኳሶችንም በማዳን ክለቡ ውጤት ይዞ እንዲወጣ ያደረገባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ነበሩ ።

ተከላካዮች

አስቻለው ታመነ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

የ2008 ዓ.ም የሊጉ ኮከብ ተጨዋች አስቻለው ታመነ በጉዳት እና በቅጣት ምክንያት በዘንድሮው የውድድር አመት ጅማሬ ላይ በብዛት በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ መግባት ያልቻለ ቢሆንም በሂደት ግን ወደቀድሞው ብቃቱ እየተመለሰ ነው። ምንም እንኳን ክለቡ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት ቢገጥመውም ተጨዋቹ በግሉ ከሳላዲን ባርጌቾ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር እንዲሁም ለቡድኑ የተከላካይ መስመር ቁልፍ ተጨዋች በመሆን እና ቦታውን በማስከበር መልካም እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።

አበበ ጥላሁን (ሲዳማ ቡና)

ለቡድኑ የመከላከል ጥንካሬ የጀርባ አጥንት ከሆኑ ተጨዋቾች አንዱ አበበ ነው። ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ በተደረጉት ጨዋታዎች ላይ ሙሉ ለሙሉ የመሰለፍ ዕድል ያገኘው የመሀል ተከላካዩ ወጥ አቋሙን እያሳየ ይገኛል። የቀድሞው የአርባምንጭ ከተማ ተጨዋች በተለይ ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ቡድኑ ግቦችን በቀላሉ እንዳያስተናግድ የበኩሉኑ አስተዋፅኦ መወጣት ችሏል።

ቢያድግልኝ ኤልያስ (ጅማ አባ ቡና)

በሁለተኛው ዙር አንድ ግብ ብቻ ላስተናገደው የጅማ አባ ቡና የተከላካይ መስመር ዋነኛ ተዋናይ የሆነው ቢያድግልኝ ኤልያስ ነው ። በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በብሔራዊ ቡድን ቆይታው በርካታ ልምድ ማካበት የቻለው ቢያድግልኝ የአባ ቡና ዋና ማገር ሆኗል። ጅማ አባ ቡና ላሳየው አንፃራዊ መሻሻል እና ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ውስጥም ዋነኛ ተጠቃሽ ነው። ከደደቢት ጋር 1-1 ከመለያየቱ በፊት በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያልተቆጠረበት የአባ ቡና ቡድን የተከላካይ መስመር ጥንካሬ ውስጥ በዋናኝነት የዚህ ተጨዋች አስተዋፅኦ የላቀ ነበር።

ሰንደይ ሙቱኩ ( ሲዳማ ቡና)

ኬንያዊው የግራ መስመር ተከላካይ ባሳለፍነው ወር ጠንካራ አቋማቸውን ካሳዩ የሲዳማ ቡና ተጨዋቾች መሀከል አንዱ ነው። ከግራ መስመር ተከላካይነት በተጨማሪ በመሀል ተከላካይነት እና በተከላካይ አማካይነት ቦታ ላይ መጫወት የሚችለው ሰንደይ ሙቱኩ በመጀመሪያ የውድድር አመቱ በሂደት ሊጉን እና ክለቡን በመላመድ የቡድኑ ወሳኝ ተጨዋች ወደመሆን ደረጃ ተሸጋግሯል። ክለቡ እያሳየ ለሚገኘው ከፍተኛ መሻሻል እና ለመከላከል ጥንካሬውም የዚህ ተጨዋች ሚና ከፍ ያለ ሲሆን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በተደረገው የመጨረሻ ጨዋታም ግብ ማስቆጠሩ የሚዘነጋ አይደለም።

አማካዮች

ኄኖክ ካሳሁን ( ጅማ አባ ቡና )

በውድድር አመቱ አጋማሽ አዳማ ከተማን ለቆ ወደ ምዕራብ የኢትዮጵያው ክለብ ያመራው ሔኖክ ካሳሁን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቡድኑ ጋር መላመድ ችሏል። በተከላካይ አማካይነት ቦታ ላይ ለክሪዝስቶም ንታንቢ እና ለአጥቂ አማካዮቹ የተሻለ የማጥቃት ነፃነትን በመስጠት በቢያድግልኝ ኤልያስ ለሚመራው የተከላካይ መስመር ጥሩ ሽፋን እየሰጠ ይገኛል። የተጨዋቹ ወደ ጅማ ማቅናትም በሁለተኛው ዙር ጅማሮ ቡድኑ እያሳየ ለሚገኘው መሻሻል በጉልህ የሚታይ መልካም ተፅዕኖ እያሳረፈ ይገኛል።

አዲስ ህንፃ (አዳማ ከተማ )

በደደቢት እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ከፍ ባለ ደረጃ ሲጫወት የምናስታውሰው አዲስ ህንፃ ከሱዳን መልስ አዳማ ከተማን ቢቀላቀልም እስከዘንድሮው የውድድር አመት አጋማሽ ድረስ ከአካል ብቃት ጋር በተያያዘ ብዙ የመሰለፍ ዕድል ማግኘት አልቻለም ነበር። ሆኖም በሳለፍነው ወር በተለይ ቡድኑ ከተፎካካሪዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል።

ትርታዬ ደመቀ (ሲዳማ ቡና)

በዘንድሮው የውድድር አመት ከሌላው የደቡብ ክለብ አርባምንጭ ከተማ መሪዎቹን መቀላቀል ከቻሉት ተጨዋቾች መሀከል አንዱ የሆነው ትርታዬ ደመቀ ከመስመር እየተነሳ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለቡድኑ ጥሩ የማጥቃት አማራጭ ሲፈጥርለት ታይቷል። ከቡድኑ ጋር ለመዋሀድ ጊዜ ያልፈጀበት ትርታዬ በመጨረሻው ጨዋታ ግብ ከማስቆጠሩ በተጨማሪም ከመስመር የሚልካቸው ኳሶች  ፣ ለግብ የሚሆኑ በርካታ ዕድሎችን ለፊት አጥቂዎቹ እየፈጠሩ ይገኛሉ።

አጥቂዎች

ጋዲሳ መብራቴ (ሀዋሳ ከተማ)

ጋዲሳ መብራቴ ሀዋሳ ከተማ አሁን ላይ እያሳየ ላለው የውጤት መሻሻል ጉልህ አስተዋፅኦ ማድረግ ችሏል ። ከሜዳ ውጪ ይነሱበት የነበሩ ጉዳዮችንም በመፍታት የቡድኑን የማጥቃት ሂደት ከመስመር በሚያደርገው እንቅስቃሴ እያገዘ ይገኛል። በውድድር አመቱ ያስቆጠራቸውን ግቦች ስድስት ማድረስ የቻለው እና  በ20ኛው ሳምንት ጨዋታም መከላከያ ላይ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ አንዱን አመቻችቶ ማቀበል የቻለው ጋዲሳ  በጠንካራ የርቀት ምቶቹ እና ተሻጋሪ ኳሶቹ ለቡድኑ ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር ይታያል።

ጌታነህ ከበደ (ደደቢት)

የፕሪምየር ሊጉን ከፍተኛ የግብ አግቢነት በ16 ግቦች እየመራ ያሚገኘው ጌታነህ ከበደ አምስቱን ግቦች ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ ነበር ያስቆጠረው። ባለፉት የሶከር ኢትዮጵያ የወሩ ምርጥ ቡድን ውስጥ ሁለት ጊዜ መካተት የቻለው ጌታነህ ከበደ እያሳየ የሚገኘው አቋም ቀጣይነት በዚህኛው ወርም እንዲካተት አድርጓል። ጌታነህ አሁንም ቡድኑ ከፈጥራቸው ጥቂት ዕድሎች በመነሳት በማይጠበቅ የጊዜ እና የቦታ አጠባበቁ እንዲሁም በአስገራሚ የአጨራረስ ብቃቱ በመታገዝ ግቦችን ማስቆጠሩን ቀጥሎበታል፡፡

ፕሪንስ ሰርቪኒሆ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ለፈረሰኞቹ ከፈረመ በኋላ በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ የመሰለፍ ዕድል አግኝቶ መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻለው ፕሪንስ ሰቭሪንሆ ከረጅም ወራት በኋላ ወደ አሰላለፍ ውስጥ መግባት ጀምሯል። አሁን አሁንም ቡድኑ ለሚታወቅበት የመስመር ጨዋታ ሁነኛ አማራጭ ሲሆን ማስተዋል ተችሏል።  ተጨዋቹ ከመስመር የሚልካቸው ኳሶች በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ለሚገኙ የፊት አጥቂዎች ጥሩ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ይስተዋላል። ምንም እንኳን በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ላይ የተወሰኑ ደቂቃዎችን ብቻ መሰለፍ ቢችልም ከዚያ በፊት በነበሩት ጨዋታዎች አራት ግብ የሆኑ ኳሶችን በማቀበል ከየትኛውም የሊጉ ተጫዋች የላቀ መሆን ችሏል ።

ተጠባባቂዎች

ጃኮ ፔንዜ

ሰይፈ መገርሳ

ደሳለኝ ደባሽ

ጋቶች ፓኖም

ኃይሌ እሸቱ

የየካቲት – መጋቢት ኮከብ ተጫዋች – ቢያድግልኝ ኤልያስ (ጅማ አባ ቡና)

የየካቲት – መጋቢት ኮከብ አሰልጣኝ – አለማየሁ አባይነህ (ሲዳማ ቡና)

3 Comments

  1. ሲዳማ 4 ተጨዋቾች በማሰመረጥ በጣም ደስ ብሎኛል! Soccer ይመቻችሁ!

Leave a Reply