ፕሪሚየር ሊግ ፡ ቻምፒዮኖቹ በአሸናፊነታቸው ቀጥለዋል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ሲቀናው አዳማ ከነማ ነጥብ ጥሏል፡፡

3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከነማ ወደ ጎንደር ተጉዞ ከዳሽን ቢራ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ፈፅሟል፡፡ አዳማ ከነማ የአቻ ውጤቱን ተከትሎ በ41 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አስቀድሞ ቻምፒዮን መሆኑን ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ብሄራዊ ሊግ መውረዱን ያረጋገጠው ወልድያን አስተናግዶ 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል፡፡ በጨዋታው መጀመርያም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቻምፒዮንነቱን ማረጋገጡን ተከትሎ ወልድያዎች በግራ እና ቀኝ በመቆም ፈረሰኞቹን በክብር አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

በጨዋው ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ወልድያዎች ሲሆኑ ማይክ ሰርጂ በ45ኛው ደቂቃ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ ግሩም ግብ አስቆጥሯል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ፈረሰኞቹ ፍፁም የጨዋታ ብልጫ ያሳዩ ሲሆን አራቱንም ግቦች ያስቆጠሩት በዚሁ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ነው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስን ግቦች ከመረብ ያሳረፉት ፍፁም ገብረማርያም (2) ፣ ምንያህል ተሾመ እና አዳነ ግርማ ናቸው፡፡

ያጋሩ