የአሰልጣኞች አስተያየት | አዲስ አበባ ከተማ 1-1 አርባምንጭ ከተማ

በ21ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ አርባምንጭ ከተማን አስተናግዶ 1-1 በሆነ ውጤት ተለያይቷል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም የቡድኖቹ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን እንደሚከተለው ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ አስራት አባተ – አዲስ አበባ ከተማ

ስለጨዋታው

” ከእረፍት በፊት የኛ ልጆች ለጨዋታው የነበራቸው ከፍተኛ ስሜት ጉጉት ውስጥ ከቷቸው ነበር ። በተጨማሪም አርባምንጭ ኤሌክትሪክን አሸንፎም ስለመጣ ተረጋግቶ ነበር የሚጫወተው ። በዚህም ብልጫ ወስደውብናል ። ከእረፍት በኋላ ግን የተወሰደብንን ብልጫ በማስተካከል የጎል ዕድሎችን ፈጥረናል ። የተሻለም መንቀሳቀስ ችለናል ። ”

ቡድኑ ውጤት ማስጠበቅ ስላለመቻሉ

” ያለንበት ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑ ለማሸነፍ ምናደርገውን ጥረት በጫና የተሞላ አድርጎታል ። ተጨዋቾችንም ወጣቶች ናቸው ። ተጋጣሚያችንም ከኛ በተሻለ የተረጋጋ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቡድን ነበር ። በጫና ውስጥ ያሉ ቡድኖች እና ከጫና ነፃ የሆኑ ቡድኖች ሲገናኙ ይሚፈጠር ነው ። ያም ሆኖ ተጨዋቾችን ቀይረን የተሻለ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረናል ። ”

ቡድኑ የመሀል ሜዳ የበላይነት ተወስዶበትም በሁለት አጥቂዎች ስለመጠቀሙ

” አርባምንጭ ባሰብነው አይነት ቅርፅ ነው የገጠመን ። ከእረፍት በፊትም አርባምንጭ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የወሰደው በተረጋጋ መንገድ ለጨዋታው በመቅረቡ ነው ። እኛ ካለንበት ደረጃ ለመውጣት ግቦችን ለማስቆጠር በርካታ አጥቂዎችን መጠቀም እና በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታን መጫወት ይጠበቅብናል ። አጥቂ ከቀነስን ግን ጨዋታችን ኳሱ ላይ ብቻ የተመሰረተ ይሆናል። ”

 አሰልጣኝ ጳውሎስ ፀጋዬ – አርባምንጭ ከተማ

ስለጨዋታው

” የጨዋታውን 90 ደቂቃ በበላይነት ነበር ያጠናቀቅነው ። ሆኖም ግን ያገኘናቸውን ብዙ አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻልንም ። ትልቁ ችግራችን ይህ ነበር ። ጨዋታውን በርግጠኝነት ለማሸነፍ አስበን ነበር የመጣነው ። ሆኖም ኳሶችን ማባከናችን ጎድቶናል ። ”

ስለ ጨዋታ መደራረብ

” ፌዴሬሽኑን በጣም ነው የምኮንንነው። ምክንያቱም ክለቦችን በዕኩል ዐይን እያየ አይደለም። ረቡዕ ተጫውተን ቅዳሜ እንድንጫወት መደረጋችን ተገቢ አይደለም ። ከኛ ጋር የተጫወቱ ሌሎች ቡድኖች ሰኞ ነው ሚጫወቱት ። ስለዚህ ፌዴሬሽኑ እየሰራ ያለው ነገር እና የፕሮግራም አውጣጡ ለኔ አልተመቸኝም ።

የወንድሜነህ ዘሪሁን እና የምንተስኖት አበራ ተጠባባቂ መሆን

” በአጨዋወት ደረጃ ከ 4- 2- 3- 1 ወደ 4- 4- 2 መጥተናል ዋናው ምክንያት ይህ ነው ። ከዛ በተጨማሪ ተከታታይ ጨዋታዎችን እያደረግን በመሆኑም ድካሞች አሉ ከዛ ከዛ የተነሳ ነው ። ”

በመጀመሪያው ግማሽ ቡድኑ ወደማጥቃት ሲሸጋገር ዝግ ያለ ስለመሆኑ

“እረፍት ሰዐት ላይ ስለዚህ ጉዳይ ተነጋግረናል። ጥሩ እንጫወታለን። ወደ ማጥቃት ክልል ውስጥ ስንገባ ግን በጣም እንቸኩላለን። ኳሶችን ተረጋግተን በመቀባበል መግባት ሳንችል ቀርተናል ። ይህንንም ወደፊት ለማሻሻል ጥረት እናደርጋለን። “

1 Comment

  1. “” ፌዴሬሽኑን በጣም ነው የምኮንንነው። ምክንያቱም ክለቦችን በዕኩል ዐይን እያየ አይደለም። ረቡዕ ተጫውተን ቅዳሜ እንድንጫወት መደረጋችን ተገቢ አይደለም ። ከኛ ጋር የተጫወቱ ሌሎች ቡድኖች ሰኞ ነው ሚጫወቱት ። ስለዚህ ፌዴሬሽኑ እየሰራ ያለው ነገር እና የፕሮግራም አውጣጡ ለኔ አልተመቸኝም ።” this is also my question?

Leave a Reply