የኢትዮጵያ ቡና የቴሌቪዥን ፕሮግራም በቅርብ ቀን እንደሚጀምር ተገለፀ

ኢትዮጵያ ቡና በኢትዮጵያ የስፖርት ክለቦች ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውንና “ቡናችን” የተሰኘውን በጄ-ቲቪ ኢትዮጵያ ላይ እየተዘጋጀ የሚቀርበው የቴሌቪዥን ፕሮግራም በቅርብ ቀን እንደሚጀምር ዛሬ በሂልተን አዲስ በተጠራው የማብሰሪያ ዝግጅት ላይ ይፋ ተደርጓል፡፡

በማብሰሪያ ዝግጅቱ ላይ የክለቡ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የደጋፊዎች ማህበር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ጥቂት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብና በጄ ቲቪ ኢትዮጵያ መካከል ለአንድ አመት የሚቆይ የውል ስምምነትም ተፈርሟል፡፡

በዚሁ ዝግጅት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ይስማሸዋ በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ የዛሬዋ እለት ለክለቡ የደስታ ቀን መሆኑን ተናግረው ይህንን የቴሌቪዥን ፕሮግራም እውን ለማድረግ እጅግ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ይህንን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለክለቡ 40ኛ የምስረታ በአል ለማድረስ የታሰበ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳኩ መቅረቱንም አቶ ይስማሸዋ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ፕሮግራሙ በተለያዩ ምክንያቶች ስታድየም መገኘት ለማይችለው እጅግ በርካታ የሆነ የክለቡ ደጋፊ ስለ ክለቡ ወቅታዊ መረጃ የሚያግኝበት ፕሮግራም እንደሚሆን ጠቁመው ፕሮግራሙ በሳምንት አንድ ቀን ማለትም ማክሰኞ ምሽት ከ2፡00- 3:00 እንዲሁም በድጋሚ ሀሙስ ቀን 6:00-7:00 በተለይ በውጪ ሀገር ለሚኖሩ የክለቡ ደጋፊዎች ሲባል እንደሚደገምም አያይዘው ገልፀዋል፡፡

የክለቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በውላቸው መሠረት በሂደት የሚታደስ ለ1 አመት የሚቆይ ሲሆን በውሉ መሠረት ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብና ጄ ቲቪ ኢትዮጵያ ከሚገኘው የስፖንሰርና የማስታወቂያ ገቢም ተጋሪ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

በመቀጠል በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ፕሬዝዳት የሆኑት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በንግግራቸው “ቡናችን” በሚል መጠርያ የሚቀርበው የክለቡ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በይፋ መከፈቱን አብስረዋል፡፡ በመቀጠልም በሬዲዮ ፕሮግራም በመክፈት ፈርቀዳጅ ስፖርት ክለብ እንደሆኑት ሁሉ በቴሌቪዥኑም ጀማሪ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ይህ ፕሮግራም በደጋፊዎቻቸው እና በክለቡ መሀል እንደ ድልድይ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልፀዋል፡፡ በመካከለኛው ምስራቅ እና በአውሮፓ ላይ ለሚገኙ በርካታ የክለቡ ደጋፊዎችም ታላቅ ብስራት ነው ብለዋል፡፡

እንደ መቶ አለቃ ፍቃደ ንግግር ከሆነ ክለቡ በቀጣይ ከ3 እስከ 4 አመት ባለ ጊዜ ውስጥ የራሱ የሆነ የቴሌቪዥን ጣቢያ የመክፈት ህልም እንዳለው የተናገሩ ሲሆን ክለቡ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በ35ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ የሚያሰነባውን 25ሺህ ሰው የመያዝ አቅም ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቀውን ስታዲየም የግንባታ ሂደት ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ እንደሚያበስር ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የጄ ቲቪ ኢትዮጵያ ማኔጀር በሆኑት አቶ ዮሴፍ ገብሬና የኢትዮጵያ ቡና ስፓርት ክለብ ስራ አስኪያጅ በሆኑት አቶ በላይ እርቁ መካከል የውል ስምምነት ፊርማ ተካሂዷል፡፡ ከስምምነቱ በኃላ ጄ ቲቪን በመወከል ፊርማቸውን ያኖሩት የቴሌቪዥን ጣቢያው መስራችና ማኔጀር የሆኑት አቶ ዮሴፍ ገብሬ እንደተናገሩት ጄ ቲቪ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በመስራቱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ጣቢያቸው አቅሙ እስከፈቀደ ድረስ ለክለቡ ፕሮግራም ፕሮዳክሽንን ጨምሮ አቅማቸው በፈቀደ መልኩ ጣቢያቸው እገዛ እንደሚያድርግላቸው ገልፀዋለል፡፡ ስፖርት ክለቡ ወደፊት የራሱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመክፈት በሚያደርገው ጥረትም ልምዳቸውን ለማካፈልና ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በፕሮግራሙ መጨረሻ የ”ቡናችን” ቴሌቪዥን ፕሮግራምን ይዘት የሚያሳይ መጠነኛ ፊልም ለእድምተኞቹ ቀርቧል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በኢትዮጵያ ስፖርት ክለቦች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሬዲዮ እና የቴሊቪዝን ፕሮግራም በመክፈት ፋና ወጊ ክለብ መሆን ችሏል፡፡

1 Comment

  1. Bravo Ethiopia Bunna! Thanks for your contribution to Ethiopian football.

Leave a Reply