19ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተያዘለት ፕሮግራም መሰረት በሳምንቱ መጨረሻ እንደማይደረግ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
በቅዱስ ጊዮርጊስ እና በኢትዮጵያ ቡና መካከል የሚደረገው ፍልሚያን ጨምሮ ሌሎች የሳምንቱ መርሃ ግብሮች የማይካሄዱት በመጪው እሁድ የኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን (ከ20 አመት በታች) ለአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ ለማለፍ ከደቡብ አፍሪካ ጋር የማጣርያ ጨዋታ ስለሚያደርግ ነው፡፡ በካፍ ህግ መሰረት የኢንተርናሽናል ውድድር የሚያስተናግድ ስታዲየም ከጨዋታው 2 ቀናት በፊት ጨዋታ እንዳይደረግበት ያዛል፡፡
መከላከያ በናይል ቤዚን ውድድር ላይ ይሳተፋል
ሴካፋ ዘንድሮ ሊጀምር ያሰበው የናይል ተፋሰስ ሃገራት የክለቦች ሻምፒዮና በሱዳን ይካሄዳል፡፡ በአባይ ተፋሰስ ሃገራት ክለቦች መካከል የሚደረገው ይኸው ውድድር ላይ ለመካፈል የ2005ቱ የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ መከላከያ ተመርጧል፡፡ በዚህም መሰረት የ19ኛ ሳምንት ጨዋታውን ከኢትዮጵያ መድን ጋር በቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ አካሂዶ ወደ ሱዳን ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አርብ አዲስ አበባ ይገባሉ
በ2015 በሴኔጋል አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ20 አመት በታች ሻምፒዮና ለማለፍ የሚደረገው የ1ኛ ዙር ማጣርያ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ይጀመራሉ፡፡ በቅድመ ማጠርያው የሲሸልስ አቻውን በድምር ውጤት 5-0 ያሸነፈው ብሄራዊ ወጣት ቡድኑ በመጪው እሁድ የ1ኛው ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታውን ደቡብ አፍሪካን በማስተናገድ ይጀምራል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ከ20 አመት በታች የልኡካን ቡድንም አርብ ጠዋት አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
መሃመድ ኢብራሂም ወደ ታዳጊ ቡድን
ስሙ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝነት ጋር በሰፊው ሲያያዝ የሰነበተው መሃመድ ኢብራሂም ‹‹ ኪንግ ›› የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ መሾሙ እየተነገረ ነው፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቡና አምበል ኪንግ እና ግብ ጠባቂው አሊ ረዲ በቅርቡ የ17 አመት በታች ቡድን አሰልጣኝ ሆነው የተሸሙት ዮሃንስ ሳህሌ ረዳቶች የመሆናቸው ነገር እርግጥ ይመስላል፡፡
የብሄራዊ ቡድኑ ረዳት አሰልጣኝ በቀጣዮቹ ቀናት ይታወቃል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው የተሸሙት ማርያኖ ባሬቶ ነገ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በመምጣት የምክትሎቻቸውን ምርጫ ያጠናቅቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የግብ ጠባቂ ፣ የአካል ብቃት እና ረዳት አሰልጣኙ ከኢትዮጵያ እንዲሆን የተስማሙት ባሬቶ 5 ስማቸው ያልተገለፁ (ሁለቱ የአካል ብቃት አሰልጣኞች ናቸው) እጩዎች ቀርበውላቸዋል፡፡
{jcomments on}