በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየም ላይ አዳማ ከተማን ያስተናገደው ወልድያ 1-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል፡፡ በበርካታ ደጋፊዎች እና ግሩም ህብረ ዜማ የታጀበው ጨዋታም ፈጣን እና ማራኪ እንቅስቃሴ ታይቶበታል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተደጋጋሚ የግብ እድል የፈጠሩ ሲሆን ዳዋ ሁቴሳ ከቅጣት ምት ሞክሮ በግቡ ቋሚ የወጣበት የመጀመርያው ሙከራ ነበር፡፡ ከደቂቃ በኋላ ደግሞ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኘው ያሬድ ሀሰን ሁለት የአዳማ ተከላካዩችን አታሎ የመታውን ኳስ ጃኮ ፔንዜ ሲተፋው አንዱአለም በግምባሩ ገጭቶ ቢሞክርም በሚያስቆጭ ሁኔታ ግብ ሳይሆን ቀርቷል።
በ15 ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው የቢሌንጌን መውጣት ተመልክቶ የሞከረውን ኳስ ቢሌንጌ እንደምንም ሲያድንበት በ23 ደቂቃ ከያሬድ ሀሰን የተሻማውን ኳስ አቤጋ እና ጃኮ ፔንዜ ተደርበው ኳሱ ሲያልፍ ያሬድ ብርሀኑ ወርቃማ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝቾ በጎሉ ቋሚ ወደ ውጭ ሊወጣ ችሏል።
ጨዋታው በተሟሟቀ ሁኔታ ቀጥሎ በ32 ደቂቃ ታፈሰ ተስፋዬ ሱራፌለልን ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ አገናኝቶት ቢሌንጌ ያዳነበት ኳስ ሌላው በመጀመርያው አጋማሽ የተፈጠረ የግብ እድል ነበር፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመርያው ሁሉ ፈጣን እንቅስቃሴ ቢስተዋልም በሙከራ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች ተቀዛቅዘው ታይተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ከሚጠቀሱ ሙከራዎች መካከል በ51ኛው ደቂቃ ዳዋ የመታውን ኳስ ቢሌንጌ ሲተፋው አዳማዎች ሞክረውት በጎሉ በላይ የወጣው እና በ60 ደቂቃ ያሬድ ሀሰን ወደ ጎል ያሻገረውን ኳስ ጃኮ ጎሉን ለቆ በመውጣቱ የተፈጠረውን አደገኛ የግብ አጋጣሚ የአዳማ ተከላካዮች ያደዳኑት ይገኙበታል፡፡
በ68 ደቂቃ አንበለሐ ዮሀንስ ኃይሉ በጥሩ ሁኔታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አንዱአለም ከጃኮ ፔንዜ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ በግሩም ሁኔታ ቺፕ በማድረግ ወሳኟን እና የጨዋታዋን ልየዩነት ፈጣሪ ጎል አስቆጥሯል።
ከዚህ ግብ በኋላ አዳማዎች ኳስን ተቆጣጥረው ጫና በመፍጠር ለመጫወት ሲሞክሩ የተስተዋሉ ሲሆን በአንፃሩ ወልድያ ከፊት ያሉትን ሁለቱን የመስመር አጥቂዎች በመከላከል ጊዜ ወደ ኋሏ እየተመለሱ ሲያግዙ እና በመልሶ ማጥቃት ፈጣን የሆነ ሽግግር ለማድረግ እና ከቢሌንጌ በሚነሱ ቀጥተኛ ኳሶችን በመጠቀም ለማጥቃት ሲጥሩ ተስተውሏል።
አዳማዎች በ72 ደቂቃ አስቆጥረው ያልፀደቀችውን ግብ ጨምሮ በ86ኛው ደቂቃ ሲሳይ ቶሊ ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ ቤሊንጌ ያዳነበትን የግብ እድል ቢፈጥሩም ጠንካራው የወልድያ የተከላካይ መስመርን መስበር ሳይችሉ ጨዋታው በወልድያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ወልድያ 27 ነጥብ ሰብስቦ ባለበት 9ኛ ደረጃ ላይ ሲቀጥል ባለፈው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን በመርታት ወደ ዋንጫው ፉክክር የገባው አዳማ መሪዎቹን ይበልጥ ለመጠጋት የሚችልበትን እድል አምክኗል፡፡
በሜዳው ጠንካራ የሆነው ወልድያ በፕሪሚየር ሊጉ ለተከታታይ 11ኛ ጊዜ ሳይሸነፍ መዝለቅ ሲችል በአጠቀላይ ከ2007 ግንቦት ወር ጀምሮ ለተከታታይ 28 ጨዋታዎች በሜዳው ሽንፈት ሳይቀምስ መጓዝ ችሏል፡፡