የጨዋታ ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ፋሲል ከተማን አሸንፏል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ሲውል ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ፋሲል ከተማን አስተናግዶ 2-0 በማሸነፍ በድንቅ መሻሻሉ ቀጥሏል፡፡

በዛሬው ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ ስታድየም ከሌላው ጊዜ በተለየ እጅግ አስደናቂ የሆነ የደጋፊ ድባብ የታየ ሲሆን ስታድየሙም በተመልካች ተሞልቶ ነበር፡፡ ረጅም ኪሎሜትር አቋርጠው የመጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፋሲል ከተማ ደጋፊዎችም በስፍራው መገኘት ችለዋል፡፡

የሀዋሳ ከተማ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት በታየበት ጨዋታ ፋሲል ከተማዎች በመሀል ሜደዳ ላይ የተገደበ እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡ ሀዋሳ ወጀ ግብ በመድረስ ቀዳሚ የነበረ ሲሆን ፍሬው ሰለሞን መሀል ለመሀል አሾልኮ የሰጣት ኳስ መድሀኔ ታደሰ ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡፡

በተደጋጋሚ ወደ ፋሲል የግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት ባለሜዳዎቹ ሀዋሳዎች በ14ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከቅጣት ምት ያሻማት ኳስ በአፄወቹ ተከላካዮች ስትመለስ ሀይማኖት ወደ ግብ በቀጥታ መትቶ የፋሲል ተከላካይ ያሬድ ባዬ ተንሸራቶ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል፡፡
እምብዛም የግብ ሙከራ መታየት ባልቻለበት የመጀመርያ አጋማሽ ፋሲል ከተማዎች ተደጋጋሚ ጥፋቶችን በግብ ክልላቸው ጥፋት ሲፈፅሙ ታይቷል፡፡ በ27ኛው ደቂቃ  ያሬድ ባዬ በረጅሙ ያሻገረውን አብዱራህማን ሙባረክ ወደ ግብ መትቶ ሶሆሆ ሜንሳህ ካዳነበት ኳስ ውጭም ተጨማሪ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡

በ37ኛው ደቂቃ ጋዲሳ ከመስመር ያሻማው ኳስ በፋሲል ተከላካይ በእጅ በመነካቷ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አማካዩ ፍሬው ሰለሞን ወደ ግብነት ለውጦ ሀዋሳ ከተማን ቀዳሚ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ ይህች ግብ ለፍሬው ዘንድሮ በሊጉ ያስቆጠራት 8ኛ ግብ ሆና ተመዝግባለች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ ተጭኖ በመጫወት የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ፋሲል ከተማ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም ተቀዛቅዞ ቀርቧል፡፡
በ68ኛው ደቂቃ የመሀል አማካዩ ታፈሰ ሰለሞን በግሩም ሁኔታ ሶስት የፋሲል ተከላካዮችን አልፎ የሰጠውን ኳስ ጃኮ አራፋት ወደ ግብነት በመቀየር የሀዋሳን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ እንደ ፍሬው ሁሉ ቶጓዊው አጥቂ ጃኮ አራፋትም በውድድር ዘመኑ ያስቆጠረው 8ኛ ጎሉ ሆነኖ ተመዝግቦለታል፡፡

ከግቡ በኋላም ሀዋሳ ከተማ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በፍሬው ሰለሞን ፣ መድሀኔ ታደሰ እና ጋዲሳ መብራቴ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ሲችል በፋሲል በኩል በ71ኛው ደቂቃ ኤደም ሆሮሶውቪ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ ቋመሚ የመለሰበት ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችሉበት እድል ነበር፡፡ ይሁንና ተጨማሪ ግቦች ሳየይቆጠሩ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

አፄዎቹ ሽንፈት ቢያስተናግዱም 1000 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው የመጡት ደጋፊዎቻቸው ለተዋሳ ድምቀት ሆነው ውለዋለል፡፡ በሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎችም መልካም የሆነ አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል፡፡

በውጤቱ መሰረት በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ መሻሻል ያሳየው ሀዋሳ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ወጥቶ ከወገብ በላይ ወዳሉ ክለቦች ግስጋሴውን ሲቀጥል ፋሲል ከተማ በሁለተኛው ዙር ካደረጋቸው 4 ጨዋታዎች 3ኛ ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡


አስተያየቶች

ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ

ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ እኛም ጥሩ ተጫውተናል፡፡ በአንደኛው ዙር ያጣናቸውን በሁለተኛው ዙር እያገኘን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ነጥብ መጣላችን አስቆጭቶን ነጥብ መሠብሠብ እየቻልን ነው፡፡ እስካሁን በሁለተኛው ዙር ከደደቢት ሽንፈት ውጭ በተከታታይ ማሸነፋችን ሙሉ በሙሉ ከስጋት እንድንወጣ አስችሎናል፡፡ ዛሬ ተጫዋቾቼ በሙሉ አቅም ተጫውተው አሸንፈዋል፡፡ ደስ የሚል አደጋገፍንም ተመልክቻለው፡፡

ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ፋሲል ከተማ
ጨዋታው በአመዛኙ ጥሩ ነው፡፡ እኛ ቅድመ ውድድር ዝግጅት እዚሁ ሀዋሳ በማድረጋችን እና ሲቲ ካፕ በመጫወታችን በቀላሉ ማሸነፍ እንችላለን ብዬ ነበር ያሰብኩት፡፡ ሀዋሳ በሜዳው ግብ ለማግባት ይዘገያል ፤ ስለሆነም በመልሶ ማጥቃት ተጫውተን ለማግባት ነበር ሀሳባችን፡፡ ጥረትም አድርገን ነበር ፤ ነገር ግን ተጫዋቾቼ በእጅ ነክተው የገባችብን ፍፁም ቅጣት ምት ያሰብነውን እንዳናደርግ አግዶናል፡፡ ይህን ያህል ርቀት ተጉዞ የመጣው ደጋፊ በውጤቱ ባይኮራም በሰጡን ድጋፍ እጅግ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡

Leave a Reply