የጨዋታ ሪፖርት | ጅማ አባቡና በሜዳው ወሳኝ ሶስት ነጥቦች አሳክቷል 

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ጅማ ላይ መከላከያን ያስተናገደው ጅማ አባቡና በጨዋታው መገባደጃ በተገኘች አጨቃጫቂ የፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅመው መከላከያን 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃቸውን ማሻሻል ችለዋል፡፡

ተመጣጣኝ የሆነ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ 45 ደቂቃ እንቅስቃሴ ጅማ አባቡናዎች በተደጋጋሚ በአሜ መሀመድ ፣ ዳዊት ማሞና ኪዳኔ አሰፋ ጫናዎችን ቢፈጥሩም ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም፡፡

በመከላከያዎች በኩል ከ7 ወራት ጉዳት ከተመለሰ በኃላ ወደ ቋሚ 11 ውስጥ ሰብሮ ለመግባት እየተቸገረ የሚገኘውና በዛሬው ጨዋታ ላይ በቋሚነት መሰለፍ የቻለው የቀድሞው የወላይታ ድቻ የአጥቂ ስፍራ ተሰላፊ የነበረው ባዬ ገዛኸኝ በግሉ ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል፡፡ ከእሱ በተጨማሪ ሌላኛው ፈጣኑ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ምንይሉ ወንድሙ በተደጋጋሚ የግብ እድሎችን መፍጠር ቢችሉም የጅማ አባቡናዎችን መረብ ግን መፈተሽ አልቻሉም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማ አባቡናዎች ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ወስደው ተጭነው መጫወት ችለዋል፡፡ በ69ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ምንይሉ ወንድሙ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመራው ፌደራል ዳኛ ሚካኤል አርአያ ለሰራው ጥፋት ቢጫ ካርድ በመዘዙበት ወቅት ባሳየው ያልተገባ ባህሪ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ በመሰናበቱ ምክንያትም ጅማዎች የበለጠ ጫና እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል፡፡

ከምንይሉ በቀይ ካርድ መሠናበት በኃላ የመከላከያው አሰልጣኝ ሻለቃ በለጠ ገ/ኪዳን ባዬ ገዛኸኝን አስወጥተው ማራኪ ወርቁን በማስገባት የማራኪን ፍጥነት በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በተለይም ማራኪ ወርቁ አስደናቂ ፍጥነቱን ተጠቅሞ አፈትልኮ ገብቶ ከሲሳይ ባንጫ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ሲሳይ ያዳነበት ኳስ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር፡፡

የጨዋታው መደበኛ ደቂቃ ሊጠናቀቅ 6 ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት ባሳለፍነው ሳምንት ቡድኑ በሀዋሳ ከተማ 3-0 ሲሸነፍ በጨዋታው ላይ በ5 ቢጫ ምክንያት መሰለፍ ያልቻለውና ዳግም በዛሬው ጨዋታ ላይ ከአወል አብደላ ጋር የመከላከያን የመሀል ተከላካይ ስፍራ ሲመራ የነበረው አዲስ ተስፋዬ በመከላከያ የግብ ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት የሶከር ኢትዮጵያ የየካቲት-መጋቢት ወር ኮከብ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው ቢያድግልኝ ኤሊያስ አስቆጥሮ ቡድኑን ለወሳኝ ሶስት ነጥብ አብቅቷል፡፡ በአንፃሩ የመከላከያ ተጫዋቾች ፍፁም ቅጣት ምቱ የተሰጠበት ሂደት አግባብ አይደለም በሚል ከዳኛው ጋር አላስፈላጊ አሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው ተስተውለዋል፡፡

ጨዋታው ለመከታተል ስታድየም ታድመው የነበሩት እጅግ በርካታ ቁጥር የነበራቸው የጅማ አባቡና ደጋፊዎች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ደስታቸውን በሰፊው ሲገልፁ ተስተውሏል፡፡

አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ የቀድሞው ክለባቸው የሆነውን መከላከያን ገጥመው ባሸነፉበት በዚሁ ጨዋታ ላይ ባስመዘገቡት ወሳኝ ድል በመታገዝ ነጥባቸውን ወደ 23 በማሳደግ በ12ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ በዘንድሮው አመት በሊጉ ለመቆየት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

2 Comments

  1. Aba Buna fans have to stop insulting and blaming players.Its now common it see fans interfering on the managerial decisions specially to replace players

  2. ለብዙ ዓመታት በPrimer League የተጫወቱ አንጋፋ የኢትዮጵያ ክለቦች ወደ ጅማ ስታድየም መጥተው ከጅማው አባቡና ክለብ ጋር ለመጫወት ሲገቡ ከመጀመርያው ደቂቃ ጀምሮ የጨዋታውን ሰዐት ለማባከን የሚያደርጉት ድርጊት ገንዘቡን ከፍሎ ጥሩ ጨዋታ ለማየት የገባውን ተመልካች ከማሳዘኑም በላይ ቀደም ሲል የጅማ ህዝብ በቴሌቪዠን ብቻ ሲመለከታቸው የነበሩና ኢትዮጵያን በዐለምአቀፍ መድረክ ወክለው ሲጫወቱ የነበሩ ቡድኖችን ዛሬ ላይ ምስጋና ለልጆቹ (ለጅማው አባቡና ክለብ) ይሁንና እዚሁ ጅማ ላይ ሊመለከታቸው ቢበቃም በተጋጣሚ ቡድኖቹ አሳፋሪ አጨዋወት የተነሳ የሀገሪቱ እግር ኳስ እየወደቀ ለመሆኑ ግንዛቤ ለማግኘት ችሏል፡፡ በነባሮቹና በአዲሶቹ ክለቦች መካከል የተለየ ነገር ባለመኖሩ አንጋፋዎቹ ክለቦች እባካችሁን አትፍሩ ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት ዳኛ መክበብና ጫና መፍጠራችሁን ወደ ጎን በማድረግ አሰልቺና አሳፋሪ አጨዋወታችሁን ትታችሁ እግር ኳስ ተጫወቱ

Leave a Reply