የጨዋታ ሪፖርት | የሳልሀዲን ሰኢድ የጭማሪ ሰአት ግብ ፈረሰኞቹን ወደ ሊጉ አናት መልሳለች

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዛሬም ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታታይ ሁለት ሳምንታት ሽንፈት በኋላ ወደ ድል በተመለሰበት የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ የሊጉ መሪ የነበረው ሲዳማ ቡናን በሳልሀዲን ሰኢድ የ90+2ኛው ደቂቃ ግብ ዳግም ወደ ሊጉ አናት ተመልሷል፡፡

በጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ባሳለፍነው ሳምንት ከሜዳው ውጪ በአዳማ ከተማ ከተሸነፈው ቡድን በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ በጉልበት ጉዳት ከሠሞኑ መሠለፍ ያልቻለው ሮበርት ኦዶንካራን ወደ መጀመርያ አሰላለፉ ሲመለስ አማካይ ስፍራ ላይ ተስፋዬ አለባቸው አዳነ ግርማን ተክቶ በተለመደው የ4-3-3 ቅርፅ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል፡፡ እንግዶቹ ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው ባሳለፍነው ሀሙስ በሀዋሳ አለምአቀፍ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡናን 3-1 ከረታው የቡድን ስብስብ ላይ የመስመር ተከላካዩ ወሰኑ ማዜን በግሩም አሰፋ ብቻ ተክተው በተመሳሳይ የ4-2-3-1 ቅርፅ ወደ ጨዋታው ቀርበዋል፡፡

የተጠበቀውን ያህል ሳቢ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ በሜዳው ላይ ይታይ ከነበረው የሁለቱ ቡድኖች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በተሻለ በሜዳው የነበሩት የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች ያሳዩ የነበረው የሞቀ ድጋፍ ቀልብን የሚገዛ ነበር፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሲዳማ ቡናዎች ከራሳቸው የግብ ክልል ኳሶችን መስርተው እንዳይወጡ ለማድረግ ሲያደርጉት የነበረው ጥረት ከሞላ ጎደል ስኬታማ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በተደጋጋሚ በጊዮርጊስ ተጫዋቾች በሚደርስባቸው ጫና የተነሳ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች በብዙ አጋጣሚዎች ኳሶችን ያለ አላማ ወደፊት ሲለጉ ተስተውሏል፡፡ በጊዮርጊስ በኩልም ለወትሮው ስለአስፈሪነቱ ይነገርለት የነበረው የመስመር አጨዋወት ባለፉት ሁለት ሳምንታት እንደታየው በዚህም ጨዋታ እጅግ ተዳክሞ ተስተውሏል፡፡

ይህ ነው የሚባል ጠንካራ የግብ ሙከራ ባልታየበትና ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንጻራዊነት በተሻለ ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም የሲዳማ ቡና የተከላካይ ስፍራ ተሰላፊዎች የሚቀመሱ አልሆኑም፡፡ በአንጻሩ ሲዳማ ቡናዎች በረጃጅሙ ከግብ ክልል ውጪ ከሚሞክሯቸው ኳሶች ውጪ ወደ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ቀርበው ሙከራዎችን ለማድረግ ሲቸገሩ ታይቷል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያውን አጋማሽ 0-0 አጠናቀው ወደ መልበሻ ቤት ባመሩበት ወቅት በተለምዶው ካታንጋና ሚስማር ተራን በሚያዋስነው አጥር ስር በነበሩ የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል መጠነኛ ግጭት ተቀስቅሶ ነበር፡፡ ነገርግን የፀጥታ ሀይሎች ስር ሳይሰድ በቶሎ ለመቆጣጠር ችለዋል፡፡

 በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ በጨዋታው ላይ እጅግ አስገራሚ የነበረው ክስተት ተከስቷል፡፡ ከ49ኛው ደቂቃ ጀምሮ የስታድየሙ ፓውዛ ሙሉ ለሙሉ በመጥፋቱ በእለቱን ጨዋታው በመሀል ዳኝነት የመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው ጨዋታውን ያለ መብራት ለ4 ያክል ደቂቃዎች እንዲቀጥል ቢያደርጉም በ53ኛው ደቂቃ ላይ ግን ጨዋታውን ለማስቆም ተገደዋል፡፡ በዚህም ጨዋታው ለ21 ደቂቃዎች ያክል ከተቋረጠ በኃላ ዳግም ሊጀምር ችሏል፡፡ ነገሩን ይበልጥ አስገራሚ ያደረገው የዚሁ እድሜ ጠገብ ስታድየም ፓውዛ ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮጲያ ቡና ከኤሌክትሪክ ባደረጉት ጨዋታ እንዲሁ በሁለተኛው አጋማሽ ላይ በመጥፋቱ ጨዋታው በተመሳሳይ ለ21 ደቂቃዎች መቀረጡ ነበር፡፡

ጨዋታው ከተቋረጠበት 53ኛው ደቂቃ በጀመረባቸው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች በተሻለ በረጃጅሙ ፊት ላይ ለሚገኙት ላኪና አዲስ በሚላኩ ኳሶች በተሻለ ወደ ጎል ለመድረስ ሞክረዋል፡፡ በተለይም በ58ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ከሮበርት ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ ተጠቃሽ ነበረች፡፡

ጨዋታው ለመጠናቀቅ እየተቃረበ በመጣባቸው የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁለቱ መስመሮች በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን ውስጥ በሚሻሙ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም የሲዳማው ግብጠባቂ ለአለም ብርሃኑ የሚቀመስ አልሆነም፡፡ ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ነው ተብሎ ሲጠበቅ በ90+2ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡና የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ልማደኛው ግብ አዳኝ ሳልሀዲን ሰኢድ ግሩም ግብ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹን ዳግም ወደ ሊጉ አናት እንዲመለሱ አስችሏል፡፡

ፈረሰኞቹ ከተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት በኃላ ወደ ድል ተመልሰው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀራቸው በ38 ነጥቦች ወደ ሊጉ አናት መመለስ ሲችሉ ሲዳማ ቡና ወደ 3ኝነት ወርዷል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

” ይሄ 3 ነጥብ ለኛ በጣም አስፈላጊያችን ነበር ። ተጨዋቾቻችን ባለፉት ሁለት ሽንፈቶች ምክንያት ከነበሩበት መንፈስ እንዲወጡ ለማሸነፍ በጣም ፈልገን ነበር ። በዛ ላይ ተጋጣሚያችን መሪ ነበር እሱንም ማስመለስ ነበረብን ። በጣም አስቸጋሪ ጨዋታ ነበር ። ሲዳማም ወደኋላ ተጠቅጥቆ በመከላከል በመልሶ ማጥቃት መጫወቱ ልናጠቃ ያሰብንበትን መንገድ አስቸጋሪ አድርጎት ነበር ። ሆኖም በመጨረሻ ጣፋጭ ይሆነ ጎል አግኝተን ማሸነፍ ችለናል ። ”

ስለሁለቱ የመስመር አጥቂዎች መቀየር

” ተጋጣሚያችን በመስመር እንደሙጠብቀን እናውቃለን ። ለዛም ነበር ምንተስኖት እና ኒኪማን ከተስፋዬ ፊት ገፍተው እንዲጫወቱ ያደረግነው ። ተጋጣሚያችን ወደኋላ በጣም በማፈግፈጉ ተጨማሪ ሀይል በመፈለግ የመስመር አጥቂዎቻችንን ቀይረናል ። በዚህም ምክንካት ጫና በመፍጠር ማሸነፍ ችለናል ። ”

አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና

ስለ ጨዋታው

” በጨወታው አጠቃላይ እንቅስቃሴም ሆነ ወደግብ በመድረስ የተሻልን ነበርን ። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ አዲስ  ዕድሎችን አባከነ እንጂ የተሻለ ተንቀሳቅሰን ነበር ። ባጠቃላይ ጊዮርጊሶች ዕድለኛ ነበሩ ማለት እችላለው ። ”

ምንም የተጨዋች ቅያሪ ስላለማረጋቸው

” ተጨዋች የሚቀየረው የደከመ ተጨዋች ሲኖር ወይም ክፍተት ሲኖር ነው ። እንዳያችሁት ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን አስራ አንዱም ተጨዋቼች ጥሩ ነበሩ ። የተሸነፍነውም በመጨረሻ ደቂቃ ላይ በሰራነው አንድ ስህተት ነው ። በጭማሪ ደቂቃ ላይ መዘናጋታችንም ዋጋ አስከፍሎናል ።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *