” ጎል የማስቆጠር አቅማችን ከዚህ በኋላ እየጨመረ ይሄዳል” አንዱአለም ንጉሴ

በወረደ በአመቱ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ወልድያ ካለፈው ሰህተቱ ትምህርት የወሰደ ይመስላል፡፡ ጠንካራ የተከላካይ መስመር እና በቀላሉ የማይሸነፍ ቡድን በመስራትም የደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡

ቡድኑ የተሻለ የውድድር አመት እንዲያሳልፍ ከረዱት መካከል አንጋፋው አጥቂ አንዱአለም ንጉሴ ይጠቀሳል፡፡ ቡድኑ ካስቆጠራቸው ጥቂት ግቦች መካከል ወሳኝ ጎሎችን ያስቆጠረው “አቤጋ” እሁድ በ21ኛው ሳምንት ወልድያ አዳማ ከተማን 1-0 ከረቱ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡

በእግርኳስ ህይወትህ የተለያዩ ክለቦች ተዟዙረህ ተጫውተሀል፡፡ ይህ በእግር ኳስ ህይወትህ የሚፈጥርብህ ስሜት ምንድን ነው?

ምንም የተለየ የሚፈጥርብኝ ስሜት የለም ስራ እስከሆነ ድረስ ተዟዙረህ ትጫወታለህ፡፡ እንደውም አዲስ ክለብ በተቀላቀልኩ ቁጥር ለእኔ ሁሌም እንደ አዲስ ነው የምሆነው። ዋናው ነገር በሄድኩበት ሁሉ ጠንክሬ በመስራት ውጤታማ መሆን ነው የምፈልገው፡፡ ያ ደግሞ እየተሳካልኝ ነው።

አቋምህን ጠብቀህ እስካሁን በሊጉ ጎል እያስቆጠርክ ነው…

አዎ ሁሌም ልምምዴን ጠንክሬ በመስራቴ ነው። ጎል የማስቆጠር አቅሜ ያልቀነሰው ልምምዴን ስሰራ ልክ ዘጠና ደቂቃ ሜዳ ገብቼ እንደምጫወተው ነው። ልምምድ ላይ ሹፈት ፣ ቀልድ አላቅም ያ ሁሌም አቅሜን ጠብቄ ጎል እንዳስቆጥር ረድቶኛል፡፡

ወልድያ ጎል የማስቆጠር ችግር አለበት፡፡ የሚገኙ ጥቂት የጎል አጋጣሚዎችንም የመጠቀም ችግር አለ፡፡ ይሄን እንዴት ታየዋለህ ?
ዝግጅት ከቡድኑ ጋር ብዙም አልሰራንም፡፡ ቀጥታ እንደመጣን ወደ ጨዋታ ነበር ያመራነው። ይህ ተቀናጅተን ለመጫወት ችግር ሆኖብናል፡፡ የአጨራረስ ችግሩም የመጣው ከዛ የተነሳ ነው። በሂደት በአሁን ወቅት ወደ ጎል እየቀረብን ነው። በጥሩ ሞራል ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን ፤ ወልድያንም በፕሪሚየር ሊጉ ማቆየት ትልቁ ስራችን ነው።

ወልድያ መከላከል ላይ መሰረት ያደረገ አጨዋወት መጫወቱ ጎል እንዳታስቆጥሩ ምክንያት መሆን ይችላል ?

ልክ ነህ፡፡ ሊጉ ሲጀመር ቡድናችን መጀመርያ መከላከልን መሰረት ያደረገ አጨዋወት ነበር የሚከተለው፡፡ የማጥቃት አጨዋዋወታችን አነስተኛ በመሆኑ ብዙ ጎል እንዳናስቆጥር አድርጎናል። አሁን ግን አማካዮች ወደ ፊት እየሄዱ ለአጥቂዎች ኳስ እያደረሱ ነው፡፡ ስለዚህ ጎል የማስቆጠር አቅማችን ከዚህ በኋላ እየጨመረ ይሄዳል ።

በፕሪሚየር ሊጉ የአዳዲስ አጥቂዎች እጥረት አለ፡፡ አሁንም በየጨዋታው ነባር አጥቂዎች ናቸው ጎል የሚያስቆጥሩት፡፡ ይህ ለወደፊት የአጥቂ ችግር በሊጉ አይኖርም ትላለህ ?

አዎ፡፡ እኔም ግራ የገባኝ ነገር ነው። በዚህ አመት ውድድር ብዙ ጎል አልተቆጠረም። አሁንም ጎል የሚያስቆጥሩት ነባር አጥቂዎች ናቸው። በፊት አዳዲስ አጥቂዎች እየመጡ እና እየተተኩ ታዳጊ አጥቂዎች ይፈጠሩ ነበር። እነሱም ወድያውኑ መጥተው ከሁለት ከአንድ አመት በኋላ አቅማቸውን እያሳዩ ትልቅ አጥቂ ይሆኑ ነበር። ለምሳሌ ከሙገር ታዳጊ አጥቂዎች ይፈጠሩ ነበር፡፡ አሁን ይህ ነገር የተቋረጠ ይመስለኛል። ይህ የአጥቂ ችግር በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

Leave a Reply