ጋና አዲስ አሰልጣኝ ሾማለች

የጋና እግርኳስ ማህበር ብሄራዊ ቡድኑን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት እንዲመራ አዲስ አሰልጣኝ መቅጠሩን ዛሬ ከሰዓት አስታውቋል፡፡ የእግርኳስ ማህበሩ የቀድሞውን አሰልጣኝ ጄምስ ክዌሲ አፒያን ዳግም በአሰልጣኝነት ቀጥሯል፡፡

እስራኤላዊው አሰልጣኝ አቭራም ግራንት በጋቦኑ የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ያስመዘገቡት ውጤት በጥቋቁር ከዋክብቶቹ ቆይታ እንዳይኖራቸው ያደረገ መሆኑን ተከትሎ የእግርኳስ ማህበሩ አዲስ አሰልጣኝ ለመቀጠር ፍለጋ ላይ ነበር፡፡ አሰልጣኝ በመቅጠሩ ሂደት ላይ ስደስት አባላት ያሉት ኮሚቴ አሰልጣኞችን የመለመለ ሲሆን ዛሬ የስራ አስፈፀሚ ኮሚቴ ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ ክዌሲ ከዚህ ቀደም ከ2012-2014 የጋና አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ቡድኑን በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ አራተኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ሲያስችሉ ለ2014 የአለም ዋንጫ ማሳለፍ ችለው ነበር፡፡ ክዌሲ ካልተሳካው የ2014 የአለም ዋንጫ በኃላ ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ተለያይተው ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ሱዳን በመምጣት የአል ካርቱም አል ዋታኒ ክለብ ሲያሰለጥኑ ቆይተዋል፡፡

የክዌሲ ምክትል ሆነው የሚሰሩ አሰልጣኞች ይፋ ባይደረጉም ከጋና እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡ የግራንት ምክትል የነበሩት ማክሱዌል ኮናዱ በስራቸው እንደሚቀጥሉ ተጠብቋል፡፡ የቀድሞ የጋና ኮከቦች የነበሩት ስቴቨን አፒያ እና ግብ ጠባቂው ሬቻርድ ኪንግስተን በብሄራዊ ቡድኑ ስራ እንሚያገኙ ተጠብቋል፡፡ ክዌሲ ከፈረንጆንቹ ግንቦት 1 ጀምሮ ስራቸውን እንደሚጀምሩ የእግርኳስ ማህበሩ ገልጿል፡፡ 

ክዌሲ ጋናን ለ2018 ቻን፣ ለ2019 የካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ለ2018 የአለም ዋንጫ ለማለፍ በቀሪ አራት ጨዋታዎች መልካም ውጤት ማስገኘት ይጠብቅባቸዋል፡፡ ጋና በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ በግብፅ እና ዩጋንዳ ተቀድማ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጋና ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሴራሊዮን ጋር መደልደሏ ይታወሳል፡፡

Leave a Reply