የጨዋታ ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚያቆየውን ድል አስመዝግቧል 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ዛሬ አዲስአበባ ስታድየም ላይ ተካሂዶ የወራጅነት ስጋት የተደቀነበት ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና 3-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ራሱን በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ማቆየት ችሏል፡፡

ሰርቢያዊውን አሰልጣኝ ኒቦይሳ ቩሲቪችን አሰናብተው አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማንና ረዳታቸው የሆነውን እድሉ ደረጀን ወደ አሰልጣኝነት መንበሩ ከሾሙ በኃላ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአስደናቂ የውጤት መጓዝ ቢችሉም ባሳለፍነው ሳምንት በሀዋሳ አለምአቀፍ ስታዲየም በሲዳማ ቡና የ3-1 ሽንፈት ማስተናገዳቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ቡናዎች በትላንትናው እለት ሲዳማን በመርታት በ38 ነጥብ አንድ ቀሪ ጨዋታ እየቀረው ሊጉን ከሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ፤ ተጋጣሚያቸው ወላይታ ድቻ ለወትሮው በሊጉ በአነስተኛ በጀት ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድንን በመገንባት የሚታወቁት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪና ቡድናቸው የወትሮው ጥንካሬያቸው ዘንድሮ ላይ ከድቷቸው የመውረድ ስጋት ውስጥ ከመገኘታቸው አንጻር ጨዋታው በእጅጉን ተጠብቆ ነበር፡፡

በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች ለተከታታይ 10 ጨዋታዎች ከዘለቀው ያለመሸነፍ ጉዞቸው ከተገታበት የሲዳማ ቡናው ጨዋታ መጠነኛ ለውጦችን በማድረግ አማካይ ስፍራ ላይ በኤልያስ ማሞ ምትክ በ5 ቢጫ ምክንያት በሐሙሱ ጨዋታ መሰለፍ ያልቻለው ጋቶች ፓኖም ወደ ቡድን ስብስቡ ተመልሶ በተመሳሳይ የ4-3-3 ቅርፅ ወደ ጨዋታው ቀርቧል፡፡

በአንጻሩ እንግዶቹ ወላይታ ድቻዎች ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ ወደ ድሬዳዋ አቅንቶ ከፍፁም የጨዋታ የበላይነት ጋር በድሬዳዋ ከተማ 2-0 ከተሸነፈው ቡድን ምንም ለውጥ ሳያደርጉ በተመሳሳይ የ5-4-1 ቅርፅ ወደ ጨዋታው መግባት ችለዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ከተጀመረበት ደቂቃ አንስቶ ወላይታ ድቻዎች ከዚህ በፊት ከሜዳ ውጪ ሲጫወቱ እንደሚያደርጉት ወደ ኃላ አፈግፍገው በመከላከል አልፎ አልፎ በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ከቻሉ ግቦችን ለማስቆጠር ካልቻሉ ደግሞ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት በማሰብ ጥቅጥቅ ብለው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ከዚህ በፊት በበርካታ አጋጣሚዎች እንደተስተዋለው ወደ ራሱ የግብ ክልል በጥልቀት የሚከላከልን ቡድን በማስከፈት በኩል ያለበት ችግር በዛሬውም ጨዋታ ላይ በጉልህ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ታይቷል፡፡

የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ ወደ ወላይታ ድቻ የሜዳ አጋማሽ አድልቶ ሊከናወን ችሏል፡፡ ነገርግን ኢትዮጵያ ቡናዎች ይህንን እጅግ የተጠቀጠቀውን የወላይታ ድቻ ቡድን ለማስከፈት የሜዳውን ስፋት ከመጠቀም ይልቅ በመሀል ለመሀል ለማስከፈት የሚያደርጉት ጥረት በቀላሉ በድቻ ተጫዋቾች ሲጨናገፍ ታይቷል፡፡ በወላይታ ድቻዎች በኩል ደግሞ በጥልቀት ከተከላከሉ በኃላ በጥቂት አጋጣሚዎች በተለይም በመጀመሪያው የቡድኑ ቅርፅ ከአምስቱ ተከላካዮች በቀኝ በኩል የውጪኛው ተከላካይ ሆኖ ጨዋታውን የጀመረው አናጋው ባደግ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ለማስጀመር ጥረት ቢያደርግም ከቡድን አጋሮቹ በቂ ድጋፍ ማግኘት ባለመቻሉ በበርካታ አጋጣሚዎች ኳሶችን ሲቀማ ተስተውሏል፡፡

 


በዚሁ በመጀመሪያው አጋማሽ ወላይታ ድቻዎች የቆሙ ኳሶችን በሚያገኙበት ጊዜ በቁጥር በርከት ብለው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት የሚሻሙትን ኳሶችን ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት ውጤታማ አልነበረም፡፡

ይህ ነው የሚባል ግልጽ የማግባት ሙከራ ባልታየበት በዚሁ በመጀመሪያው አጋማሽ በ4ኛው ደቂቃ ላይ ወላይታ ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ በጨዋታው በዲቻዎች በኩል ብቸኛ የፊት አጥቂ የነበረው ተመስገን ዱባ ከኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪስን ጋር ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡ በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል በ31ኛው ደቂቃ ላይ መስኡድ መሀመድና አማኑኤል ዮሀንስ በአንድ ሁለት ቅብብል ከገቡ በኃላ መስኡድ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ ተጠቃሽ ነበረች፡፡ በዛሬው ጨዋታ ላይ የአስቻለው ግርማን አለመኖር ተክቶሎ በአዲስ ሚና በግራ መስመር የአጥቂነት የተሰለፈው አማኑኤል ዮሀንስ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ በተደጋጋሚ አደጋ ለመፍጠር ሲጥር ተስተውሏል፡፡

በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወደ መሀል ሜዳ ጠጋ ብሎ ሲከላከል የነበሩትን የወላይታ ድቻ ተከላካዮች ከጀርባቸው ትተው የሚሄዱትን ክፍተት ለመጠቀም በማሰብ በረጃጅሙ ኳሶችን ወደፊት በሚጥሉበት ወቅት የወላይታ ድቻ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች በአስደናቂ ንቃት ወደ ኃላ በማፈግፈግ ሲያጨናግፉባቸው ታይቷል፡፡ ሌላኛው በዚሁ በመጀመሪያው አጋማሽ ከተከላካይ አማካዩ ጋቶች ፓኖም ፊት በግራና በቀኝ የተሰለፉት አቡበከር ናስር እና መስኡድ መሀመድ እንደፈለጉትን በነጻነት ኳሶችን እየተቀበሉ እንዳያደረጁ ወላይታ ድቻዎች ከአምስቱ ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾቻቸውና ከፊት ለፊታቸው በሚገኙት አራት ተከላካዮች መካከል የሚገኘውን ስፍራን በማጥበብ አነዚህ ተጫዋቾች በባህሪያቸው የሚፈልጉትን በመስመሮች መሀከል የሚፈጠረውን ክፍተት እንዳያገኙ በማድረግ በኩል የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ አቡበከር ነስሩን አስወጥተው አክሊሉ ዋለልኝን በማስገባት ተቀይሮ የገባው አክሊሉን ከተከላካዮች ፊት እንዲቆም በማድረግ ጋቶች ፓኖምን በ4-3-3 ቅርጽ ከተከላካይ አማካዮ ፊት ካሉት ሁለቱ አማካዮች የቀኙን ስፍራ እንዲያዝ አድርገው ሁለተኛውን አጋማሽ ጀምረዋል፡፡

ይህ ቅያሬያቸው በደቂቃዎች ልዩነት ፍሬ አፍርቶ በ47ኛው ደቂቃ ላይ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የማጥቃት ነጻነት የተሰጠው ጋቶች ፓኖም በግሉ ጥረት ወደፊት ይዞት የሄደውን ኳስ ለቀኝ መስመር ተከላካዩ አብዱልከሪም መሀመድ ያቀበለውንና አብዱልከሪም አሻምቶ በወላይታ ድቻ ተከላካዮች ስህተት የተገኘችውን ኳስ የግብ ክልሉ ጠርዝ ላይ ይገኝ የነበረው አምበሉ መስኡድ መሀመድ በግራ እግሩ በግሩም ሆኔታ ግብጠባቂው ወንደሰን አሸናፊ በቆመበት ማራኪ ግብን አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ቻለ፡፡

ከግቧ መቆጠር ሶስት ያክል ደቂቃዎች በኃላ በ50ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ አብዱልከሪም መሀመድ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ዳግም አምበሉ መስኡድ መሀመድ ባልተለመደ መልኩ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ማሳደግ ችሏል፡፡ ለወትሮው በእርጋታው የሚታወቀው አመለ ሸጋው መስኡድ መሀመድ ሁለተኛውን ግብ ካስቆጠረ በኃላ መለያውን በማውለቁ ቢጫ ካርድ ተመልክቷል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ተከታታይ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የአጨዋወትና የተጫዋቾች የሚና ለውጥ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በዚህም ዮሴፍ ደንገቶንና ፀጋዬ ብርሃኑን አስወጥተው ጥላሁን በቶንና አማኑኤል ዮሀንስን አስገብተው የጨዋታ ቅርፃቸውን ወደ 3-4-3 በመቀየር ፊት ላይ በዛብህ መላይንና በመጀመሪያው አጋማሽ የመስመር ተከላካይ የነበረው አናጋው ባደግን በቀኝና የግራ መስመር አጥቂነት እንዲሁም ተመስገን ዱባን በፊት አጥቂነት በመጠቀም ግብ ለማግኘትና ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሞክረዋል፡፡ በዚህ የጨዋታ ቅርጽ ለውጥ ዲቻዎች ከመጀመሪያው በተሻለ በርከት ብለው ከመጀመሪያው አጋማሽ በመጠኑ ለቀቅ ባለ አጨዋወት ወደፊት ለመሄድ ቢሞክሩም ይህ ነው የሚባል የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም፡፡

ከግቦቹ መቆጠር በኃላ በነበሩት ጥቂት ደቂቃዎች ጨዋታው በመጠኑ መነቃቃት ቢታይበትም ደቂቃዎች በቆጠሩ ቁጥር ዳግም ጨዋታው መቀዛቀዝ ታይቶበታል፡፡ በጨዋታው 63ኛ ደቂቃ ጀምሮ በስታዲየሙ በቁጥር በርከት ብለው እንደወትሮው ቡድናቸውን በደማቅ ሁኔታ ሲያበረታቱ የቆዩት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እጅግ አስገራሚ የሆነ የስልክ መብራት ትርኢትን በስታዲየሙ ለማሳየት ችለዋል፡፡

ከግቦቹ መቆጠር በኃላ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው መጫወት ቢችሉም አብዛኛዎቹ የኳስ ቅብብሎች ያለ አላማ በሚመስል መልኩ በመሀል ሜዳ ላይ ተገድቦ በአመዛኙ የጎንዬሽና የኃልዮሽ የኳስ ቅብብሎች በርከት ብለው ታይተዋል፡፡

በ76ኛው ደቂቃ ላይ አሰልጣኝ መሣይ ከዚህ ቀደም ዋንኛ የቡድኑ ጎል አዳኝ የሆነውን አላዛር ፋሲካን በበዛብህ መለዬ ተክተው በማስገባት ከተመስገን ዱባ ጋር በማጣመር ወደ 4-4-2 ቅርጻቸውን መቀየር ችለዋል፡፡ አሰልጣኝ መሳይ በዚሁ ሁለተኛ አጋማሽ በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ሚና ለውጦችን ቢደርጉም ቅያሬያቸው ያን ያህል ውጤታማ አልነበሩም ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በመጀመሪያው አጋማሽ የመሀል አማካይ የነበረው ፈቱዲን ጀማል በሁለተኛው አጋማሽ የመስመር አማካይ እንዲሁም የመስመር ተከላካይ ሆኖ መጫወት ችሏል ሌላው አናጋው ባደግ መጀመሪያ ጨዋታውን ሲጀምር ከአምስቱ ተከላካዮች በቀኝ በኩል ውጨኛው ተከላካይ ሆኖ ጨዋታውን ቢጀምርም በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መስመር አጥቂ አድርገው ለመጠቀም መሞከራቸው እንደማሳያ መውሰድ ይቻላል፡፡

ወላይታ ድቻዎች በሁለተኛው አጋማሽ በተደጋጋሚ የግለሰብና የሚና ለውጦችን በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት ስኬታማ አልነበረም፡፡ ይባስ ብሎ ተቀይሮ የገባው አጥቂው አላዛር ፋሲካ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ በቃሬዛ በመውጣቱ የመጨረሻዎቹን ጥቂት ደቂቃዎች የተጫዋች ቅያሬዎችን በመጨረሳቸው በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል፡፡

ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ተብሎ በሚጠበቅበት ሰአት አክሊሉ ዋለልኝ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ጋቶች ፓኖም ከግቡ በግምት 25 ሜትር ርቀት ላይ በቀጥታ አክርሮ በመምታት አስቆጥሮ ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና የ3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ይህንን ውጤት ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡናዎች ነጥባቸውን ወደ 35 አሳድገው በ4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችሉ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ድቻዎች ወደ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ገብተዋል፡፡


2 Comments

  1. I have watched the game ,the analysis that you have done is great. Regarding Wolaita Dicha F.C, it is true as the capacity of the team is getting declining due to low attacking power.However I would like to confirm that Wolaita Dicha will never descend to lower division. Dicha will get recovered soon.

Leave a Reply