ዝውውር | ዋሊድ አታ ወደ ኖርዌይ ሊያመራ ነው

በየካቲት ወር የሳውዲ አረቢያው ናጅራን ስፖርት ክለብን የተቀላቀለው ኢትዮጵያዊው የመሃል ተከላካይ ዋሊድ አታ ወደ ኖርዌይ ሊያመራ መሆኑ ታውቋል፡፡ ዋሊድ እምብዛም የመጫወት እድል ያላገኘበት የሳውዲ አንደኛ ዲቪዝዮን ክለብ የሚለቀው እስከ ሃምሌ ድረስ በሚቆይ የውሰት ውል ነው፡፡

የ30 ዓመቱ ተከላካይ የኖርዌይ ሊግ ክለብ ወደሆነው ሳግንዳል የውሰት ዝውውሩን እንደሚያደርግ ለሶከር ኢትዮጵያ ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ “አዎ በውሰት ዝውውር ወደ ሶግንዳል ለማምራት ከጫፍ ደርሻለው፡፡ ስለዝውውሩ የተነሱ ጉዳዮችም እውነት ናቸው፡፡ በሳውዲ ሊጉ ሊጠናቀቅ አራት ጨዋታዎች ናቸው የቀሩት፡፡ ስለዚህም ባለው የሶስት ወር ጊዜ ወደ ሌላ ክለብ ሄጄ መጫወት እችላለው፡፡ እስከሚቀጥለው የውድድር ዓመት ድረስ ሊያስመዘግቡኝ ስለማይችሉ ዝውውሩን ለማድረግ ወስኛለው” ብሏል ዋሊድ፡፡

የሳግንዳል ክለብ ሃላፊ የሆኑት ሃቫርድ ፍሎ የዋሊድን የውሰት ውል ለማጠናቀቅ ሁሉም ነገሮች መጠናቀቃቸውን ለnettavisen.no በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡ “ሁሉም ነገሮች ለዋሊድ ዝውውር ተዘጋጅተዋል፡፡ አሁን ላይ የተጫዋቹ በሳውዲ ያለውን ነገር እስከሚጨርስ ነው የምንጠብቀው፡፡ የፓስፖርት ጉዳዮች እና አንዳንድ የወረቅት ስራዎች እስካልተጠናቀቁ ድረስ ዋሊድ መጫወት አይችልም፡፡”

ፍሎ ሲቀጥሉ የዋሊድ ክለባቸውን መቀላቀል ልምዱን ለታዳጊ ተጫዋቾች ለማካፈል እንደሚረዳቸው ጠቁመዋል፡፡” እሱ ብዙ ጥሩ የሆኑ ልምዶች ባለቤት ነው፡፡ ካለው ልምድ ተነስተ ለሌሎች በእሱ ቦታ ለሚሰለፉ ተጫዋቾች ጥሩ ልምድ እንደሚያስገኝላቸው እምነት አለን፡፡”

ዋሊድ የቱርኩን ገንሰርበሊጊን በ2015 መጨረሻ ከለቀቀ በኋላ ሳግንዳል ሶስተኛ ክለቡ ነው፡፡ የዋሊድ ክለብ ናጅራን ወደ ሳውዲ አረቢያ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት አሁንም ያልተሟጠጠ እድል አለው፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡ መሪዎቹን አል ፋያህ እና ኦሆድ ክለብን ተከትሎ በ37 ነጥብ በአል ነሃድ ክለብ በግብ ክፍያ ተበልጦ አራተኛ ነው፡፡

ዋሊድ ሊያመራበት የተዘጋጀው ሶግንዳል በ1926 የተመሰረተ ሲሆን በኖርዌይ ሊግ የተሻለ ስኬት ባይኖረውም ከ2011 ወዲህ በሊጉ መቆየት ችሏል፡፡ በውድድር አመቱ መክፈቻ ጨዋታ በሳርስቦርግ 08 ሲሸነፍ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታውን ከስታቤክ ፉትቦል ጋር ዛሬ ምሽት ያደርጋል፡፡ ዋሊድም የዝውውር ጉዳዮቹን በቶሎ መጨረስ ከቻለ በዛሬው ጨዋታ ላይ ለመሰለፍ ብቁ ይሆናል ተብሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *