በፊፋ ወርሃዊ የሃገራት ደረጃ ኢትዮጵያ አሽቆልቁላለች

በፊፋ ኮካኮላ የወርሃዊ የሃገራት ደረጃ ከጨዋታዎች የራቀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ማሽቆልቆልን አሳይቷል፡፡ በነሃሴ 2008 መጨረሻ ሲሸልስን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሃዋሳ ላይ 2-1 ዋሊያዎቹ ከረቱ በኃላ አንድም ጨዋታ ሳያደርጉ ቆይተዋል፡፡

የፊፋ ካላንደርን ተጠቅሞ የአቋም መለኪያ ጨዋታ አለማድረጉን ተከትሎ ብሄራዊ ቡድን በፈረንጆንቹ ሚያዚያ ወር ከዓለም 124ኛ ሆናለች፡፡ ከአንድ ወር በፊት ወደ 100 ለመግባት ተቃርቦ የነበረው ቡድን አሁን ላይ ከፍተኛ መውረድን አሳይቷል፡፡ 20 ደረጃዎችን የወረደው ቡድኑ 265 ነጥቦች አግኝቷል፡፡ ከወር በፊት በ335 ነጥብ 104ኛ ነበር፡፡

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የተደለደሉት ጋና (45ኛ)፣ ኬንያ (78ኛ) እንዲሁም ሴራሊዮን (113ኛ) ሆነዋል፡፡ በተለይ ጌረቤታችን የሆነችው ኬንያ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ማድረግ መቻሏ በደረጃዋ ላይ ከፍተኛ መሻሻል እንድታሳይ አስችሏታል፡፡ የሃራምቤ ከዋክብቶቹ ከሳምንታት በፊት በአቋም መለኪያ ጨዋታ ማቻኮስ ላይ ከዩጋንዳ አቻ ስትለያይ ዲ.ሪ. ኮንጎን በሚካኤል ኦሉንጋ ሁለት ግቦች ማሸነፍ ችለዋል፡፡

የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚ የነበረችው ግብፅ የአፍሪካ 1ኛ ሆናለች፡፡ ፈርኦኖቹ ከዓለም 19ኛ ናቸው፡፡ ሴኔጋል ከዓለም 30ኛ ከአፍሪካ 2ኛ፣ ካሜሮን ከዓለም 33ኛ ከአፍሪካ 3ኛ፣ ቡርኪናፋሶ ከዓለም 35ኛ ከአፍሪካ 4ኛ፣ ናይጄሪያ ከዓለም 40ኛ ከአፍሪካ 5ኛ ሆነው ይከተላሉ፡፡

የ2018 የዓለም ዋንጫ ተሳታፊነቷን ያረጋገጠችው ብራዚል የደረጃው አናት ላይ ተቀምጣለች፡፡ አርጀንቲና፣ ጀርመን፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጄየም፣ ፖርቹጋል፣ ስዊዘርላንድ እና ስፔን ከ2-10 ያለው ደረጃ ይዘዋል፡፡

Leave a Reply