ሐሙስ ምሽት በተደረገ የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አል አሃሊ ፔትሮጀትን 2-0 በመርታት መሪነቱን አጠናክሯል፡፡ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ሽመልስ በቀለ ከጉዳት መልስ የመጀመሪያ ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ በመግባት አድርጓል፡፡
ሽመልስ በጥር ወር በዓመቱ መጀመሪያ አጋጥሞት ከነበረው ጉዳት ለመዳን ተጨማሪ ቀዶ ጥገና ያደረገ በመሆኑ ሳምንታት ከጨዋታ ርቆ ቆይቷል፡፡ በአል አሃሊው ጨዋታ ከጉዳት መልስ የመጀመሪያ ጨዋታውን በሁለተኛው አጋማሽ 59ኛው ተቀይሮ በመግባት ማድረግ የቻለው፡፡ በጨዋታው የካይሮው ሃያሎቹ ወደ ግብ በመድረስ በተለይ በመጀመሪያው 45 ከተጋጣሚያቸው ተሸለው ታይተዋል፡፡ ጫና ፈጥረው ሲጫወቱ የነበሩት አሃሊዎች በቅርቡ ባስፈረሙት ኮትዲቯራዊው የፊት መስመር ተሰላፊ ሱሌማን ኩሊባሊ ግብ ታግዘው 1-0 መምራት ችለዋል፡፡
ከእረፍት መልስ ፔትሮጀት ወደ ጨዋታ የሚመልሰውን የአቻነት ግብ ለማግኘት ኳስን ተቆጣጥሮ ቢጫወትም ያልተደራጀው የመሃል ክፍሉ ለሃሰን ሺአታው ክለብ ነገሮችን አስቸጋሪ አድርጎበታል፡፡ ሽመልስ በዚህው ክፍለግዜ ናስር መሃርን ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ የአሃሊን ሁለተኛ ግብ ዋሊድ ሱሌማን ግብ ጠባቂውን ሄሳም ሃሰንን በማለፍ ከመረብ አዋህዷል፡፡
ሊጉን አሁንም አል አሃሊ በ58 ነጥብ ሲመራ ምስር ኤል ማቃሳ በ51 ይከተላል፡፡ በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ የሆነው ኤል መስሪ በ43 ሶስተኛ ሲሆን አዲስ አሰልጣኝ ከፖርቹጋል ያስመጣው ዛማሌክ አንድ ቀሪ ጨዋታ እየቀረው በ40 ነጥብ አራተኛ ነው፡፡ ፔትሮጀት በ33 ነጥብ ስድስተኛ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት በዋዲ ደግላ የ5-1 ሽንፈት እንዲሁም ከአስዋን ጋር 1-1 የተለያየው የኡመድ ኡኩሪው ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ከወራጅ ቀጣው በ7 ነጥብ ከፍ ብሎ በ22 ነጥብ 13ኛ ነው፡፡
በ22ኛ ሳምንት ጨዋታ በሚቀጥለው ቅዳሜ ሚያዚያ 7 ፔትሮጀት ኢትሃድ አሌክሳንደሪያን በሜዳው ሲያስተናግድ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ኤል ዳክልያን ከሜዳው ውጪ እሁድ ሚያዚያ 8 ላይ ይገጥማል፡፡