ፕሪምየር ሊግ | በአአ ስታድየም የዛሬ ውሎ ደደቢት እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸንፈዋል

 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ዛሬ አአ ስታድየም ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ደደቢት እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጋጣሚዎቻቸውን በተመሳሳይ 3-0 ውጤት አሸንፈዋል፡፡

08፡30 ላይ አዲስ አበባ ከተማን የገጠመው ደደቢት 3-0 በማሸነፍ 20ኛ አመት የምስረታ በአሉን በድል አክብሯል፡፡ ለሻቻምፒዮንነት የሚፎካከር እና ላለመውረድ የሚታገል ቡድን በተገናኙበት ጨዋታ አብዛኛው ሰዐት ማራኪ የጨዋታ ፍሰት ባይታየም ደደቢት በመጀመሪያው ግማሽ ከ 25 እስከ 29ኛው ደቂቃ በጌታነህ ከበደ ሁለት እና በሮበን ኦባማ አማካኝነት አስቆጥረው የመጀመርያውን አጋማሽ በ3-0 መሪነት አጠናቀዋል፡፡ ጌታነህ ከበደ 17ኛ እና 18ኛ ጎሎቹን በማስቆጠር የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ሰንጠረዥ መምራቱን ቀጥሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ደደቢቶች ተጨማሪ ጎል ለማቆጠር ቢጥሩም በማጥቃት ወረዳው ላይ ብዙ ያልተሳኩ ቅብብሎች ማድረጋቸው ውጤቱ እንደነበረ እንዲያልቅ አድርጎታል። አዲስ አበባ ከተማዎች በበኩላቸው ለአጥቂዎቻቸው ኳሶችን ለማድረስ ቢጥሩም የወትሮው የመሀል ሜዳ የበላይነታቸውን አብሯቸው ባለመሆኑ በጨዋታው ላይ የተለየ ተፅዕኖ መፍጠር አልቻሉም ።

ውጤቱን ተከትሎ ከትላንት በስቲያ 20 አመቱን የደፈነው ደደቢት ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነጥብ ሲስተካከል አአ ከተማ ወደ ሰንጠረዡ ግርጌ ተመልሷል፡፡

በመቀጠል የተደረገው የኤሌክትሪክ እና የመከላከያ ጨዋታ የተሻለ ፉክክር ታይቶበት በኤሌክትሪክ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ኤሌክትሪኮች ገና በ3ኛው ደቂቃ በኢብራሂም ፍፋና አማካይነት ቀዳሚ መሆን ሲችሉ በ28ኛው ደቂቃ ላይ የጦሩ የመሀል ተከላካይ አወል አብደላ በሙሉአለም ጥላሁን ላይ በሰራው ጥፋት በቀይ ወጥቷል።

ከእረፍት መልስ ኤሌክትሪኮች በፍፁም ገ/ማርያም አማካይነት በፍፁም ቅጣት ምት በ47ኛው እንዲሁም በጨዋታ በ86ኛው ደቂቃ ላይ ሁለት ግቦችን በማከል ጨዋታውን በሶስት የግብ ልዩነት ድል ማድረግ ችሏል። የግብ መጠኑን 11 በማድረስ ጌታነህ ከበደን በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ፉክክር ላይ እየተከተለ የሚገኘው ፍጹም ሶስተኛ ግብ ለማከል ከፍተኛ ጉጉት ቢታይበትም በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ ሲሆን ተስተውሏል።

ውጤቱን ተከትሎ ኤሌክትሪክ ይበልጥ ከወራጅ ቀጠናው መራቁን ሲቀጥል መከላከያ በአንጻሩ የወራጅ ቀጠናው ደጃፍ ደርሷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *