ፕሪምየር ሊግ | ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ሲጥል ሲዳማ ከመሪው በነጥብ ተስተካክሏል

 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ዛሬ ሲካሄዱ የሊጉ ቻምፒዮንነት እና ላለመውረድ የሚደረጉት ፉክክሮች ይበልጥ አጓጊ መልክ የሚይዙባቸው ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

 

ወላይታ ድቻ 1-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ወደ ሶዶ ያቀናው የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዳነ ግርማ ጎል 1-0 በመምራት ወደ መልበሻ ክፍል ቢያመራም ተከላካዩ አብዱልሰመድ አሊ በ59ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ባለሜዳዎቹን አቻ አድርጋለች፡፡ ውጤቱን ተከትሎ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተከታዩቹ ጋር ያለውን ርቀት ቢያጠብም በ39 ነጥቦች በግብ ልዩነቶች በልጦ በመሪነቱ ቀጥሏል፡፡ በአንፀሩ ወላይታ ድቻ በ23 ነጥቦች ወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመቆየት ተገዷል፡፡

ሲዳማ ቡና 2-1 ወልድያ

ባለፈው ማክሰኞ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ግብ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፎ መሪነቱን ያስረከበው ሲዳማ ቡና ወልድያን 2-1 በማሸነፍ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን ልዩነት በማጥበብ በነጥብ ተስተካክሏል፡፡ ወልድያ አንዱአለም ንጉሴ በሚታወቅበት የግንባር ኳስ የቀድሞ ክለቡ ላይ አስቆጥሮ ወልድያ የመጀመርያውን አጋማሽ በመሪነት ማጠናቀቅ ችሎ ነበር፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ አዲስ ግደይ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተሰራበት ጥፋት የተገኘውን አጨቃጫቂ የፍፁም ቅጣት ምት ናይጄርያዊው ላኪ በሪለዱም ሳኒ ወደ ግብነት ቀይሮ ባለሜዳዎቹን አቻ አድርጓል፡፡ በ68ኛው ደቂቃ ደግሞ አማካዩ ሙሉአለም መስፍን ከርቀት አክርሮ በመምታት ሲዳማ ቡና 3 ነጥብ ያስመዘበበትን የ2-1 ድል እንዲያሳካ አድርጓል፡፡

 

አዳማ ከተማ 2-2 ሀዋሳ ከተማ

አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው አዳማ ከተማ በጭማሪ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክር እና ውዝግብ በተስተናገደበት ጨዋታ ሱራፌል ዳኛቸው ከአዲስ ህንፃ የተሻገረለትን ኳስ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ቢያደርግም ከ2 ደቂዎች በኋላ ቶጓዊው ጃኮ አራፋት ታፈሰ ሰለሞን የተሸገረለትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ሀዋሳን አቻ አድርጓል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ጃኮ አራፋት ከጋዲሳ የተላከለትን ኳስ አስቆጥሮ ሀዋሳ 2-1 እየመራ እረፍት ወጥተዋል፡፡ ጃኮ በውድድር ዘመኑ ለሀዋሳ ከተማ ያስቆጠረውን ግብ 10 በማድረስ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ፉክክር ውስጥ መካተት ችሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አዳማዎች ውጤቱን ለመቀልበስ ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱ ሲሆን ጨዋታውን የመሩት ኢንተርናሽናል አርቢቴር ዘካርያስ ግርማ ውሳኔዎች ፣ የሱሌማን መሀመድ እና ሶሆሆ ሜንሳህ ግጭት ፣ ጨዋታው ለ16 ደቂቃ መቋረጥ ፣ የተጨመረው ደቂቃ እና የተጫወቱት ደቂቃ አለመመጣጠን እንዲሁም የአደማ ከተማ ደጋፊዎች በአሰልጣኝ ተገኔ አሰፋ ላይ ያሳዩት ተቃውሞ የሁለተኛው አጋማሽ ክስተቶች ነበሩ፡፡ በተለይ በ81ኛው ደቂቃ ሱሌይማን መሀመድ እና ሶሆሆ ሜንሳህ የፈጠሩት ግጭት ሁለቱንም ለቀይ ካርድ ዳርጓቸዋል፡፡

ጨዋታው በዚህ መንገድ ቀጥሎ በሀዋሳ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ ተብሎ ሲጠበቅ ሞገስ ታደሰ ወደ ግብ የማታው ኳስ ለማዳን የተንሸራተተው ወንድማገኝ ማዕረግ ገጭቶ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠር ጨዋታው 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

 

አርባምንጭ ከተማ 0-2 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ አርባምንጭ ተጉዞ ውድ 3 ነጥቦችን በመሰብሰብ ላለመውረድ የሚደርገውን ትግል አጠናክሯል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ ያለግብ በተጠናቀቀበት ጨዋታ የእንቅስቃሴ ብልጫ የነበራቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ62ኛው ደቂቃ በናይጄርያው ፒተር ኑዋዲኬ እንዲሁም በ81ኛው ደቂቃ በጂብሪል አህመድ ግቦች ታግዞ 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ድሉን ተከትሎም ነጥቡን 19 በማድረስ 13ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ጅማ አባ ቡና ጋር ያለውን ልዩነት ወደ 4 ማጥበብ ችሏል፡፡

 

ፋሲል ከተማ 2-1 ጅማ አባ ቡና

ፋሲል ከተማ አፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ጅማ አባ ቡናን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል፡፡ ጅማ አባ ቡና ከቅጣት በተመለሰው መሀመድ ናስር የ8ኛደቂቃ ጎል ቀዳሚ መሆን ቢችልም ከ5 ደቂቃዎች በኋላ ሙሉቀን ታሪኩ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ግብ አስቆጥሮ ፋሲልን አቻ አድርጓል፡፡ ከእረፍት መልስ ደግሞ አብዱራህማን ሙባረክ ፋሲልን 3 ነጥብ ያስጨበጠች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በፋሲል 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ውጤቱ ለገብረመድህን ኃይሌው ጅማ አባ ቡና በሁለተኛው ዙር የተመዘገበ የመጀመርያ ሽንፈትነው፡፡

 

Leave a Reply