የጨዋታ ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን በመርታት ወሳኝ ሶሰት ነጥብ ሰብስቧል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ወደ ድሬዳዋ ያቀናው ኢትዮጵያ ቡና ከፍተኛ እልህና አስገራሚ የደጋፊዎች ድባብ በታየበት ጨዋታ የመውረድ ስጋት የተጋረጠበት ድሬዳዋ ከተማ 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብን መውሰድ ችለዋል፡፡

ከጨዋታው አስቀድሞ ለወትሮውም ቢሆን የፍቅር ሀገር እንደሆነች የሚነገርላት የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ አቋርጠው ወደ ከተማቸው ከ10 በላይ በሆኑ አውቶብሶችና በተለያዩ የግል መኪኖች የመጡትን የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን ከከተማው በጥቂት ኬሎ ሜትር ርቀት ከሚገኘው ደንገጎ ከተሰኘው ቦታ ጀምሮ የከተማዋን የፍቅር ከተማነት ባስመሰከረ መልኩ ጥሩ የሚባልን አቀባበል ማድረግ ችለዋል፡፡

በዛሬው እለትም ከተጠባቂው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በፊት ከተቋቋመ እጅግ ጥቂት ጊዜን ያስቆጠረው የድሬዳዋ ከተማ ስፓርት ክለብ የደጋፊ ማህበር አባላት ከኢትዮጵያ ቡና አቻቸው ጋር አስናዝ ጨዋታ ማድረግ ችለዋል በዚህም የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር አመራሮች 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል፡፡

ከቀኑ 5:30 ጀምሮ ወደ ስታዲየሙ መትመም የጀመሩ ሲሆን የድሬዳዋ ስታዲየምም በዛሬው ጨዋታ ከአፍ እስከ ገደፉ በበርካታ የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ተጨናንቆ ተስተውሏል፡፡

ከሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መጀመር በፊት የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች 600ሺህ ብር ወጪ በማድረግ ለክለቡ የደጋፊዎች መለያን ስፓንሰር ያደረገውን ቱሬ ሲሚንቶንና መለያውን አሰርቶ በማቅረብ እገዛ ላደረገው አንድ የከተማው ወጣት የምስጋና ሽልማት አበርክተዋል፡፡

በጨዋታው ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት ከሜዳው ውጪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 0-0 ከተለያየው ቡድን አማካይ ስፍራ ላይ አምሀ በለጠን እወጥተው ይሁን እንደሻውን ብቻ ተክተው በ4-4-2 ቅርፅ ሲቀርቡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው ማክሰኞ ወላይታ ድቻን 3-0 ከረታው የቡድን ስብስባቸው ውስጥ አቡበከር ናስርን በአክሊሉ ዋለልኝ በመተካት በተመሳሳይ 4-3-3 ቅርፅ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል፡፡

አዲስ ባሰሩት ብርቱካናማ በነጭ መለያ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳ የገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች የመጀመሪያዋን ግብ ለማስቆጠር ሰከንዶች ብቻ ነው የፈጀባቸው የቀድሞው የኢትዮጵያ መድን ጎል አዳኝ የሆነው ሀብታሙ ወልዴ የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች በትኩረት ማነስ የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ በረከት ይሳቅ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ሀብታሙ ወልዴ ግሩም የሆነች ግብን አስቆጥሮ ድሬዎችን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን በመቆጣጠር በድሬዳዋ ከተማዎች የግብ ክልል በርካታ ኳሶችን መቀባበል ቢችሉም ይህ ነው የሚባል ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በ8ተኛው ደቂቃ አብዱልከሪም መሀመድ ወደ መሀል ያሻማውን ኳስ ሳኑሚ ተንሸራቶ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት እንዲሁም በ13ተኛው አማኑኤል ዮሀንስ ያሻማውን መስኡድ መሀመድ በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጪ ከወጣባቸው ኳስ ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም፡፡

በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማዎች በዝርግ 4-4-2 ቅርፅ ፊት ላይ ሁለቱ አጥቂዎች ከፊት ከሌሎቹ የቡድን ተጫዋቾች ተነጥለው ብቻ ቀርተው ሌሎቹ ተጫዋቾች ሁለት የመከላከል መስመርን በመስራት በአመዛኙ መሀል ለመሀል ሲመጣ የነበረውን የኢትዮጵያ ቡናን የማጥቃት እንቅስቃሴን በመመከት በኩል የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡

በኢትዮጵያ ቡና የጨዋታ የበላይነት ጨዋታው ቀጥሎ በነበረበት ሂደት በ20ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ሱራፌል ዳንኤል የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮችን ቀንሶ ያቀበለውን ጣጣውን የጨረሰ ኳስ የጨዋታው ኮከብ የነበረው ሀብታሙ ወልዴ በቀላሉ ደገፍ አድርጎ በማስቆጠር የድሬዳዎችን መሪነት ማሳደግ ችሏል፡፡

ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኃላ የጨዋታ መንፈስ ተቀይሮ ጨዋታው እጅግ እልህ የበዛበት ሽኩቻዎችና በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተቀያሬ ወንበር ላይ የነበሩ የቡድን አባላት ከፍተኛ የሆነ አለመረጋጋቶች በስፋት የታየበት ሆኗል፡፡

በ36ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው በረከት ይሳቅ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ለሀብታሙ ቢያቀብለውም ሀብታሙ ሀትሪክ ሊሰራበት የሚችልበትን አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

በዚሁ የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ በውሰት ለድሬዳዋ ከተማ እየተጫወተ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቡናው ዮሴፍ ዳሙዬ ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል፡፡

በ42ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ዮሀንስ ለመስኡድ መሀመድ በግሩም ሆኒታ በድሬዳዋ ተጫዋቾች መሀከል ያቀበለውን ኳስ መስኡድ መሀመድ ከሳምሶን አሰፋ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ኢትዮጵያ ቡናዎችን ወደ ጨዋታው ልትመልስ የምትችል ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ የኢትዮጵያ ቡናው የመሀል ተከላካይ ወንድይፍራው ጌታሁን ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ በኢኮ ፌቨር ተቀይሮ ሊወጣ ችሏል፡፡

ሌላው በዚሁ በመጀመሪያው አጋማሽ በተለምዶ በአዲስ አበባ ስታዲየም መቀመጫ አጠራር ካታንጋ በሚባለው ስፍራ የነበሩ የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች በኢትዮጵያ እግርኳስ ባልተለመደ መልኩ በመሀከላቸው የሚለይ ምንም የፀጥታ ሀይል ሳይኖር ጎን ለጎን የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች የየራሳቸውን ቡድን ሲያበረታቱተበት የነበረው መንገድ በሌሎችም ክለብ ደጋፊዎች ዘንድ ሊለመድ የሚገባ ነገር ነው፡፡

ከእረፍት መልስ ድሬዳዋ ከተማዎች ልዩነቱን ሊያሰፉበት የሚችሉበትን አጋጣሚ ከማእዘን የተሻማውን ኳስ ጋናዊው የተከላካይ አማካይ ኢማኑኤል ላሪያ በግሩም ሆኔታ ገጭቶ ቢሞክርም ሀሪስን በአስደናቂ ሆኔታ ሊያድንበት ችሏል፡፡

በመጀመሪያውም እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ በድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች በኩል በተደጋጋሚ የዳኝነት ውሳኔን ሲቃወሙ ተስተውሏል፡፡

ከመጀመሪያው ደብዘዝ ያለ በነበረው የሁለተኛው አጋማሽ 63ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ዘነበ ከበደ አክርሮ በመምታት አስደናቂ ግብን አስቆጥሮ ለማንሰራራት ተስፋ ሰንቀው በነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ስሜት ላይ ውሃ መቸልስ ችሏል፡፡

ሽኩቻዎች በበረከቱበት የሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም የድሬዳዋ ከተማው የመስመር ተከላካይ ሄኖክ አዱኛ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል፡፡ ተጫዋቾቹ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ በእለቱ ጨዋታውን የመሩት ኢንተርናሽናል አልቢትር አማኑኤል ሀይለስላሴ ፊሽካቸውን በሚያሰሙበት ወቅት ጋቶች ፓኖም ሜዳ ውስጥ መለያውን አውልቆ ጨዋታውን ከመሩት አልቢትር አማኑኤል ጋር ለተጠብ ተጋብዞ ለያዝ ለገላጋይ ሲያስቸገር ተስተውሏል፡፡

ከዚህ ክስተት ቀደም ብለው በነበሩት ደቂቃዎች በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ በተለሞዶ የቀኝ ጥላፎቅ አካባቢ የነበሩ የተወሰኑ የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች ጋቶች ፓኖም ላይ እጅግ አስነዋሪ የሆኑ ስድቦችን ሲሰነዝሩ ተደምጠዋል፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች በጎዶሎ ልጅ ጥሩ መንቀሳቀስ ቢችሉም የሽንፈትን ፅዋን ሊጎነጩ ግድ ሆኗል፡፡

በሁለተኛው ዙር ጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኝ የሚመስሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ነጥባቸውን ወደ 25  አሳድገው በ13ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችሉ  ቡናዎች 35 ነጥብ ላይ በመርጋት በቻምፒዮንነት ፉክክሩ ላይ የሚያደርጉት ጉዞ ላይ ውሃ ቸልሰዋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየቶች

ዘላለም ሽፈራው- ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታው

” እጅግ ጥሩ የሚባል ጨዋታን ማሳየት ችለናል፡፡ ምንም እንኳን ቡድናችን ጥሩ ሆኔታ ውሰጥ ባይገኝም በሁለተኛው ዙር ጥሩ መሻሻሎችን ማሳየት ችለናል፡፡ ከ3-1 ውጤቱ በዘለለ ቡድናችን በጨዋታ እንቅስቃሴ በልጦ በማሸነፉ ተደስቻለው፡፡በግሌ በ6 አመታት የማሰልጠን ጎዞዬ እስካሁን በኢትዮጵያ ቡና በሜዳዬ አልተሸነፍኩም ይህም በግሌ በጣም ደስ የሚያሰኝ ሪከርድ ሲሆን እንደ አጠቃላይ ያገኘነው ውጤት በጣም የሚገባን ነው፡፡”

ድሉ በቀጣይ ቡድኑ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽእኖ

“በሁለተኛው ዙር ቡድናችን ጥሩ መነቃቃት ውስጥ ይገኛል ፤ ይህንን መንፈስ በማስቀጠል ለተሻለ ውጤት እንሰራለን፡፡”

የደጋፊው ድባብ

“ማንኛውም ቡድን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ጨዋታ በሚያደርግበት የትኛውም ክልል ላይ የሚኖረው የስታዲየም ድባብ ልዩ ነው፡፡በተለይም ድሬዳዋ ከተማ   ውስጥ በርካታ ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች አሉ ምክንያቱም ህዝቡ እግርኳስ ወዳድ ህዝብ ነው ፤ በዚህም የተነሳ ጥሩ የወንድማችችነት ደጋፍ ልናይ ችለናል፡፡”

 

ገዛኸኝ ከተማ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው ጥሩ ቢሆንም በራሳችን በሰራናቸው ስህተቶች ዋጋ ከፍለናል፡፡ ቡድናችን ለዋንጫ እንደመጫወቱ በቀጣይ ጠንካራ ጨዋታዎች ከፊታችን አሉ ፤ በነዛም ጨዋታዎች ላይ የዛሬው አይነት ስህተቶች አርመን እንቀርባለን፡፡”

ስለ ድሬዳዋ ከተማ ደጋፊ

“እኔ የዚህ አይነት ድርጊት ሲገጥመኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በተለይ ከደጋፊዎች ይሰማ የነበረው አፀያፊ ስድብ ተጫዋቹን ለእንደዚህ አይነት ድርጊት እንዳረገው እስብለሁ ፤ ምክንያቱም በአንድ ሀገር ላይ እየኖርን ለአንድ ተጫዋች ተገቢ አይደለም፡፡ሁላችንም ኢትዮጵያውያን እንደመሆናችን እንደ ኢትዮጵያዊነት የምንቀበለው ድርጊት አይደለም፡፡ልጁ ሀገርንም ጭምር መጥቀም የቻለ ተጫዋች ነው ምንም እንኳን እግርኳስ ስሜታዊ የሚያደርግ ስፓርት ቢሆንም ያንን ከግምት በማስገባት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባ ነበር፡፡ከድሬዳዋ ህዝብ ይህን መሰል ነገር በመስማቴ አዝኛለሁ፡፡”

Leave a Reply