በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢን አል ስዊዝ ስታዲየም ላይ ያስተናገደው ፔትሮጀት ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡ በጨዋታው ላይ ኡመድ ኡኩሪ ለኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ሙሉ 90 ደቂቃ ሲሰለፍ ሽመልስ በቀለ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ገብቶ መጫወት ችሏል፡፡
ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ከወራጅ ቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ ፔትሮጀት ደግሞ ከሰሞሃ እና ከዛማሌክ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥብቦ በሚቀጥለው አመት ለካፍ ኮንፌድሬሽን ለመሳተፍ አስፈላጊ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ያደረጉት ጨዋታ ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በጨዋታ እንቅስቃሴም ይሁን ወደ ግብ በመሞከር ተሽለው የታዩት እንግዶቹ የነበሩ ሲሆን መሃሙድ ፋታላህ ከቅጣት ምት በጨዋታው ጅማሬ የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት ከደቂቃዎች በኃላ ኡመድ በግንባሩ የገጨው ኳስ በግቡ አናት ወጥቶበታል፡፡ በ25ኛው ደቂቃ ኡመድ በጥሩ መልኩ ያሻገረለትን ኳስ ኦማር ኤል ሳይድ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ከዘጠኝ ደቂቃ በኃላ የኤል ሃርቢ ተከላካይ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ናይጄሪያዊው የፔትሮጀት አጥቂ ጄምስ ኦዎቦስኪኒ ክለቡን ቀዳሚ የሚያደርግበትን ጥሩ አጋጣሚ አምክኗል፡፡
በ43ኛው ደቂቃ በኤል ሃርቢ ቀኝ መስመር ላይ ኡመድ ኳስን በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ቅጣት ምት በአግባቡ የተጠቀሙት ባለሜዳዎቹ ቀዳሚ የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል፡፡ ሃምዲ ፋቲ ግብ ጠባቂው አምር መሃመድ ያመከነውን ኳስ በቅርብ ርቀት አስቆጥሮ ለእረፍት በፔትሮጀት መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ፔትሮጀት ኳስን በመቆጣጠር የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ሻበልዲን አህመድ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ኡመድ ኡኩሪ ግብ ጠባቂው አሊ ፋራግን ጭምር በማለፍ የአቻነቷን ግብ በ57ኛው ደቂቃ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ኡመድ በሊጉ ያስቆጠራቸውን የግቦች መጠን ወደ 6 ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡
በ65ኛው ደቂቃ ፔትሮጀት ዳግም መሪ የምታደርገውን የፍፁም ቅጣት ምት ዲያቤ ሲያመክን ከ10 ደቂቃዎች በኋላ ሽመልስ በቀለ ኦዎቦስኪኒን ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡
የጨዋታው መገባደጃ አካባቢ ላይ ይህ ነው የሚባል የግብ እድል ሁለቱም ክለቦች ሳይፈጥሩ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡ የአቻ ውጤቱን ተከትሎ ፔትሮጀት በ34 ነጥብ በነበረበት ሲረጋ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በ23 ነጥብ 13ኛ ነው፡፡ ከኢትሃድ አሌክሳንደሪያ ጋር ጨዋታ ያለው አል አሃሊ አሁን ሊጉን በ58 ነጥብ ሲመራ ምስር ኤል ማቃሳ በ54 ይከተላል፡፡ አል መስሪ በ43 ነጥብ ሶስተኛ ሲሆን በኤንፒ ያልተጠበቀ ሽንፈትን የቀመሰው ዛማሌክ እና ሰሞሃ በእኩል 40 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 4ኛ እና 5ኛ ናቸው፡፡ የምስር አል ማቃሳውን አህመድ ኤል ሼክ በ14 ግቦች የኮከብ ግብ አግቢነቱን ይመራል፡፡