የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሀሙስ ጨዋታዎች – ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከነገ ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ድረስ ይደረጋል፡፡ ነገም ደርቢዎች ፣  በዋንጫው እና ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ 6 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ፋሲል ከተማ

08:30 ላይ በሳምንቱ የመጀመርያ መርሀ ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፋሲል ከተማን አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ያስተናግዳል፡፡ ኤሌክትሪክ እና ፋሲል በ22ኛው ሳምንት በቅደም ተከተል መከላከያ እና ጅማ አባ ቡና ላይ ድል ማስመዝገብ መቻላቸው የሚታወስ ነው፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለተኛው ዙር የተሻሻለ አቋም ይዞ መቅረብ ሲችል ከአንድ የሜዳ ውጪ ሽንፈት በስተቀር ከጨዋታዎች ነጥቦች ይዞ በመውጣት ከወራጅ ቀጠናው በመራቅ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ መቅረብ ችሏል፡፡ ፋሲል ከተማ በአንጻሩ ወጥ ባልሆነ አቋሙ በመዝለቅ ከደረጃ ሰንጠረዡ አናት ተፎካካሪነት ወደ ወገብ ለማሽቆልቆል ተገዷል፡፡

የቡድን ዜናዎች

በጨዋታው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የአምበሉ አዲስ ነጋሽን ግልጋሎት በጉዳት የማያገኝ ሲሆን የፋሲል ከተማው ሰለሞን ገብረመድህንም ከጨዋታው ውጪ የሆነ ተጫዋች ነው፡፡

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ፋሲል ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ተሳትፎ ያደረገው በ2000 እና ዘንድሮ የውድድር ዘመን ነው፡፡ በዚህም 2 ጊዜ ተገናኝተው አንዱን ያለግብ በአቻ ውጤት ሲለያዩ ሌላኛውን ኢትዮ ኤሌክትሪክ 3-1 አሸንፏል፡፡

ዳኛ

ጨዋታውን ፌዴራል አርቢትር ዳዊት አሳምነው የሚመራው ይሆናል፡፡

አርባምንጭ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

09:00 ላይ በአርባምንጭ ስታድየም የሚደረገው ጨዋታ በሰንጠረዡ ወገብ ከሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ይልቅ ወሳኝነቱ ለድሬዳዋ ከተማ የጎላ ነው፡፡ በ22ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን 3-1 በመርታት ከመውረድ ስጋት በመጠኑም ፋታ ያገኘው ድሬዳዋ ከተማ በሁለተኛው ዙር በእንቅስቃሴ እና ውጤት ረገድ መሻሻል አሳይቷል፡፡ ሆኖም ከሜዳ ውጪ በሚያደርጋቸው ጨዋታው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ይዘውት የሚቀርቡት የጨዋታ አቀራረብ 3 ነጥብ እንዳያሳካ እንቅፋት የሚፈጥርበት ይሆናል፡፡

አርባምንጭ ከተማ በሁለተኛው ዙር ከተዳከሙ ክለቦች አንዱ ሆኗል፡፡ በሜዳው አንድ ድል ብቻ ያስመዘገበው አርባምንጭ በ22ኛው ሳምንት ግርጌ ላይ ይገኝ በነበረው ኢትዮጵያ ንግደድ ባንክ መሸነፉም ያለበትን አቋም የሚያመለክት ነው፡፡

የቡድን ዜናዎች

አንድነት አዳነ ከ5 ቢጫ ቅጣት ወደ መጀመርያ አሰላለፍ እንደሚመለስ ሲጠበቅ በድሬዳዋ በኩል የተጫዋች ጉዳት የለም፡፡

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ሁለቱ ክለቦች በሊጉ በ2004 ፣ 2008 እና ዘንድሮ በአጠቃላይ 5 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ አርባምንጭ ከተማ 2 ፣ ድሬዳዋ ከተማ 1 ድል ሲያስመዘግቡ 2 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል፡፡ አርባምንጭ ከተማ 5 ጎሎች ሲያስቆጥር ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 1 አስቆጥሯል፡፡ ዘንድሮ በመጀመርያው ዙር ድሬዳዋ ላይ በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አርባምንጭ አማኑኤል ጎበና በ90ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል 1-0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው፡፡

ዳኛ

ይህን ጨዋታ ፌዴራል አርቢቴር ጌቱ ተፈራ ይመራዋል፡፡

ወልድያ ከ ወላይታ ድቻ

ወልድያ በመሀመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድየም ያለመሸነፍ ጉዞውን ለማስጠበቅ በማለም ነገ 09:00 ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናግዳል፡፡ ወላይታ ድቻ ባለፈው ሳምንት የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን ነጥብ ቢያስጥልም የሌሎች ቡድኖች ማሸነፍ ራሱን በወራጅ ቀጠናው ውስጥ እንዲያገኘው አስገድዶታል፡፡

በ2006 ወደ ፕሪምየር ሊጉ ካደገ ወዲህ አስከፊውን ጉዞ እያደረገ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ከጨዋታው ነጥብ ይዞ የመውጣትን ግዴታ ይዞ ወደ ሜዳ የሚገባ ሲሆን ካለፉት አመታት ተቀዛቅዘው የታዩት የቡድኑ ደጋፊዎችም ወደ ወልድያ መጓዛቸው ቡድኑን ሊያነቃቃው ይችላል፡፡

በውድድር ዘመኑ በሜዳው የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ በሚያስመዘገበው ውጤት በደረጃ ሰንጠረዡ ተረጋግቶ የሚገኘው ወልድያ በጥሩ የጎል ማስቆጠር አቋሙ ላይ የሚገኘው አንዱአለም ንጉሴ ላይ እምነቱን ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የቡድን ዜናዎች

ወልድያ የወሳኙ የመሀል ተከላካይ ያሬድ ዘውድነህን ግልጋሎት በ5 ቢጫ ምክንያት የማያገኝ ሲሆን ወላይታ ድቻ ቶማ ስምረቱን በጉዳት ያጣዋለል፡፡ ነገር ግን አላዛር ፋሲካን ከጉዳት መልስ ያገኘዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ሁለቱ ክለቦች በ2007 እና ዘንድሮ 3 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ወላይታ ድቻ 2 ፣ ወልድያ 1 ድል ሲያስመዘግቡ ወልድያ 1 ፣ ወላይታ ድቻ 3 ጎል አስቆጥረዋል፡፡

ዳኛ

ፌዴራል አርቢቴር ሳህሉ ይርጋ ይህን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራዋል፡፡

ጅማ አባ ቡና ከ አዳማ ከተማ

ጅማ አባቡና ከወራጅ ቀጠናው የመራቅ አላማን ይዞ አዳማ ከተማን 10:00 ላይ በጅማ ስታድየም ይገጥማል፡፡ ጅማ አባ ቡና በ22ኛው ሳምንት ወደ ጎንደር ተጉዞ በፋሲል ከተማ የሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ሽንፈቱን ያስተናገደው ጅማ አባ ቡና በሜዳው በሚያደርገው ጨዋታ ቀድሞ ወደነበረበት ጥንካሬ የተመለሰ ይመስላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሜዳው ውጪ የሚቸገረው አዳማ ከተማን መግጠሙ ተጠቃሚ ሊያደረገው ይችላል፡፡

በ22ኛው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ የሜዳ ሽንፈት ከማስተናገድ ለጥቂት የተረፈው አዳማ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ካሸነፈ በኋላ ወደ ዋንጫው ፉክክር ቢመለስም በተከታታይ በጣላቸው ነጥቦች ወደ ኋላ ቀርቷል፡፡

የቡድን ዜናዎች

ክሪዚስቶም ንታንቢ ከ5 ቢጫ ቅጣት በኋላ ወደ ስብስቡ እንደሚመለስ ሲጠበቅ በጅማ አባ ቡና በኩል የተጫዋች ጉዳት የለም፡፡ በአዳማ በኩል ደግሞ ሱሌይማን መሀመድ በቅጣት ፣ ብሩክ ቃልቦሬ በጉዳት ለነገው ጨዋታ አይደርሱም፡፡ ምኞት ደበበ ደግሞ ከጉዳት መልስ ጨዋታ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ጅማ አባ ቡና የመጀመርያ የውድድር ዘመን እያሳለፈ እንደመገኘቱ ሁለቱ ቡድኖች የተገናኙት አንድ ጊዜ (1ኛ ዙር) ብቻ ነው፡፡ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ የተደረገውን ጨዋታ አዳማ ከተማ በዳዋ ሁቴሳ ግብ 1-0 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

ዳኛ

ኢንተርናሽነናል አርቢቴር ባምላክ ተሰማ ከኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ መልስ ይህን ጨዋታ የሚመራው ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ደደቢት ፣ ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና የሚያደርጓቸውን ጨዋታዎች የተመለከተ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ ከቆይታ በኋላ ይዘን እንመለሳለን፡፡

2 Comments

  1. Please who is the record holder for high score in the ethiopian premier league history. How many goals did he score? thanks

Leave a Reply