“ተስፋ አልቆረጥኩም አሁንም የሊጉ ኮኮብ ግብ እስቆጣሪ መሆን እችላለው፡፡” ፊሊፕ ዳውዝ

ናይጄሪያዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጥቂ ፊሊፕ ዳውዝ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18 ጎሎች የኮኮብ አግቢነትን ከሀገሩ ልጅ ሳሙኤል ሳኑሚ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦል፡፡ ፊሊፕ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡
ስለኮኮብ ግብ አግቢነት
ተስፋ መቁረጥ አልችልም፡፡ ተስፋ አልቆረጥኩም አሁንም የሊጉ ኮኮብ ግብ እስቆጣሪ መሆን እችላለው፡፡ ተስፋ ብቆርጥ ኖሮ ሲዳማ ቡናን ለመግጠም ወደ ይርጋለም ባልተጓዝኩ ነበር፡፡ አሁንም የኮኮብ ግብ አግቢ የመሆን ብቃቱ አለኝ፡፡ በእግርኳስ የሚከሰተውን አታውቅም፡፡ ኤልክትሪክ ሃዋሳ ከነማን 6ለ0 ያሸንፋል ብሎ ያሰበ ሰው የለም ስለዚህ የኔም የኮኮብ ግብ አስቆጣሪ የመሆን ዕድል ገና አልጨለመም፡፡
ስለጠንካራ ጎኑ
የኔ ጠንካራ ጎን ይህ ነው ይህ ነው አልልህም፡፡ ጠንካራ ጎኔ የክለብ ጓደኞቼ ናቸው፡፡ ከነሱ ጋር ባለኝ የተሻለ ግንኙነት፣ መግባባት እና መረዳዳት ነው ግቦችን ላስቆጥር የቻልኩት፡፡ ካስታወስክ ዑመድ ዑኩሪ በ16 ግብ ኮኮብ ግብ አግቢ ሲሆን ተፎካካሪ አልነበረውም፡፡ አሁን እኔ፣ ሳሚ እና ቢኒያም ተፎካካሪ በመሆናችን ሁላችንንም ጠንካራ አድርጓናል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡
ስለሳሙኤል ሳኑሚ
ሳሚ በጣም ጎበዝ ተጫዋች ነው፡፡ 22 ግብ ማስቆጠሩ አልገረመኝም፡፡ ችሎታው እና ብቃቱ እንደነበረው አውቅ ነበር፡፡ ከሱ ገና ብዙ ነገር እጠብቃለው፡፡ ከዚህ የተሻለ የማድረግ አቅም አለው፡፡

ያጋሩ