“አሁን ላይ እንደቡደን መጫወት መቻላችን ጥንካሬን አላብሶናል” አራፋት ጃኮ

ሀዋሳ ከተማ ከአንደኛው ዙር መጨረሻ አንስቶ ያሳየው መሻሻል ከወራጅ ቀጠናው በፍጥነት እንዲወጣ አስችሎታል፡፡ በእስራኤል እና ሩስያ መጫወት የቻለው የቡድኑ የፊት አጥቂ አራፋት ጃኮም ከቡድኑ ጋር በጥሩ አቋም ላይ ይገኛል፡፡ 10 ግቦችን ከመረብ ያሳረፈው አራፋት ስለሀዋሳ መሻሻል እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሀዋሳ በሁለተኛው ዙር በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻልን ያሳየ ክለብ ነው፡፡ ለዚህ መሻሻል ዋነኛ ምክንያት ምንድነው ትላለህ?

እኔ እንደማስበው ከሆነ ጠንካራ፣ የተሻለ እና ውጤታማ ስራ መስራታችን ነው ለመሻሻላችን ምክንያት የሆነው፡፡ አሁን ላይ እንደ ቡድን ነው የምንጫወተው፡፡ ይህም ለመሻሻላችን መሰረት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተጫዋቾች የግል ብቃት ላይ የተመሰረተ ቡድን ነበረን፡፡ አሁን ላይ እንደቡደን መጫወት መቻላችን ጥንካሬን አላብሶናል፡፡”

በመከላከሉ ረገድ ሀዋሳ ተሻሽሏል ግብ በማስቆጠሩም አሁንም ጠንካራ ናችሁ. . .

“በመጀመሪያው ዙር በመከላከሉ ላይ በተደጋጋሚ ዋጋ ያስከፈሉንን ስህተቶች እንሰራ ነበር፡፡ ይህንንም አሰልጣኛችን (ውበቱ አባተ) በሚገባ ስለተረዳው ስህተቶች የመቀነስ ስራ ነበር የሰራነው፡፡ አሁን ላይ የተከላካይ ክፍላችን ተሻሽሏል፡፡ በማጥቃቱ በኩል በመጀመሪያው ዙር በብዛት ግብ ስላስቆጠርን ችግር አልነበረብንም ፤ ስለዚህም በጥንካሬያችን ቀጥለናል፡፡”

በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ቆይታህ 10 ግቦችን እስካሁን ማስቆጠር ችለሃል፡፡ በእቅድነት የያዝከው የግብ መጠን አለ?

“ስመጣ ከ10 በላይ ግቦች ለማሰቆጠር አቅጄ ነበር፡፡ አላማዬ 12 ግቦችን በውድድር አመቱ ለማስቆጠር ነበር፡፡ አሁን ላይ 11 ግቦች አሉኝ፡፡ (በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የፀደቀው የአራፋት የግብ መጠን 10 ነው፡፡) አሁን ባለው ሁኔታ ካቀድኩት በላይ ግብ እንደማስቆጥር አምናለው ከፊት ባለን ጨዋታዎች እና ሁኔታዎች ቢወሰኑም፡፡”

በመጀመሪያው ዙር በአብዛኛው ኳስን ለማግኘት የፊት መስመሩን እየተውክ ወደ ኋላ ትመለስና ከግቡ ትርቅ ነበር፡፡ በሁለተኛው ዙር ላይ ይህንን ነገር እምብዛም አልተመለከትንም፡፡ የግብ መጠንህ መጨመሩ ከዚህ ጋር ተያያዥ ነው?

“በመጀመሪያው ዙር አስቸጋሪ ነበር ፤ ምክንያቱም ከቡድኑ ጋር ተቀናጅቼ ለመጫወት ግዜ ፈጅቶብኛል፡፡ የቡድን አጋሮቼ እኔ ያለኝን የአጨዋወት ስልት እና የእነሱን ማጣጣም አልቻልንም ነበር፡፡ ለዚህ ነው ኳስን ለማግኘት ቦታዬን እየተውኩ ወደ ኃላ እመለስ የነበረው፡፡ ቅንጅት ሲመጣ ግን ይህንን ለማድረግ አስፈላጊ አልነበረም ስለሆነም የማስቆጥራቸው የግብ መጠኖች በርክተዋል፡፡”

ለዋንጫ ከሚፋለመው ሲዳማ ቡና ጋር የደርቢ ጨዋታ አላችሁ. . .

“ደርቢ ሁሌም ደርቢ ነው፡፡ ሁሌም ደርቢ ቀላል ጨዋታዎች አይደሉም፡፡ ጨዋታው ለሲዳማ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም እኛ በሜዳችን እና ደጋፊያችን ፊት ነው የምንጫወተው፡፡ እነሱ ለሊግ ዋንጫ ነው የሚፎካከሩት እኛም ከወራጅ ቀጣናው ብንርቅም ነጥቦችን ሰብስበን ይበልጥ ከስጋት ነፃ መሆንን ስለምንፈልግ ጨዋታን ማሸነፍ አለብን፡፡ ለጨዋታው በቂ ዝግጅት አድርገናል፡፡”

Leave a Reply