የጨዋታ ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0-1 ፋሲል ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ 08:30 ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ፋሲል ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በፋሲል ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ጨዋታው በስራ ቀን እና ሰአት ከመካሄዱ አንጻር በርካታ ተመልካች ባይገኝም የፋሲል ከተማ ደጋፊዎች በግራ የካታንጋ ክፍል ተሰብስበው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ውለዋል፡፡

ፈጣን እንቅስቃሴ በታየበት የጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም በኩል ግለልጽ የግብ ማስቆጠር አጋጣሚዎች መፈጠር አልቻሉም፡፡ ተጫዋቾች በተናጠል ፍጥነታቸውን በመጠቀም የተከላካይ መስመሩን ለማስከፈት ጥረት ከማድረጋቸው በቀር ይህ ነው የሚባል የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ በሁለቱም ቡድኖች በኩል አልተመለከትንም፡፡

በ10ኛው ደቂቃ ሙሉአለም ጥላሁን ከግራ መስመር በፍጥነት ወደ ውስጥ በመግባት የሞከረውን ኳስ ተከላካዮች ያወጡበት እንዲሁም በ20ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ከራሱ የግብ ክልል ጀምሮ በአስደናቂ ሁኔታ እስከ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ድረስ በመግፋት ያሻገረውን ኳስ ሱሌይማን ቀድሞ ያዳነው ኳስ በሁለቱ በኩል ሊጠቀሱ የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

 

ሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመርያው ሁሉ በፈጣን እንቅስቃሴ የተሞላ ሲሆን የተሻለ የግብ ሙከራ እና አሸናፊውን የለየች ጎልም አስተናግዷል፡፡

በ52ኛው ደቂቃ አምበሉ ኄኖክ ገምቴሳ ቀኝ መስመር በረጅሙ ያሻማውን ኳስ ቶጓዊው አጥቂ ኤደም ኮድዞ ሆሮሶውቪ በግንባሩ ገጭቶ ከመረብ በማሳረፍ ፋሲል ከተማን አሸናፊ ያደረገች ጎል ማሳረፍ ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኋላ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የእንቅስቃሴ ብልጫ ቢያሳይም ብልጫቸውን ወደ ግብ ሙከራነት መለወጥ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በ74ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ፍጹም ገብረማርያም በግንባሩ ገጭቶ ቴዎድሮስ ጌትነት ካዳነበት ኳስ ውጪም በኤሌክትሪክ በኩል የተደረጉት ሙከራዎችን የፋሲል ከተማ ተከላካዮች በቀላሉ ሲቆጣጠሩት ተስተውሏል፡፡

በአንጻሩ ፋሲል ከተማዎች ወደኋላ አፈግፍገው በመከላከል የአብዱራህማን ሙባረክን ክህሎት እና ፍጥነት በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎችን መሞከር ችለዋል፡፡ በተለይ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ተቀይሮ የገባው ገዛኸኝ እንዳለ ከአብዱራህማን የተሻገረለትን ያለቀለት ኳስ ያመከነው እና ከደቂቃ በኋላ አብዱራህማን ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን በመግባት ሞክሮ ለጥቂት የወጣበት ኳስ የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ጨዋታው በፋሲል ከተማ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ አጼዎቹ በአዲስ አበባ ስታድየም ያለመሸነፍ ሪከርዱን ይዞ ሲቀጥል ነጥቡን 35 በማድረስ ወደ ጥሩ አቋሙ መመለስም ችሏል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

የኢትዮ-ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ

በሁለታችንም በኩል የነበረው እንቅስቃሴ ማሸነፍን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ክፍት ነበር ጨዋታው አጥቅተን ውጤት ይዞ ለመውጣት ነው ጥረት ያደረግነው፡፡ ግን የመጀመሪያው 10 እና 15 ደቂቃዎች ላይ የተገኙትን እድሎች መጠቀም አልቻልንም፡፡ እዛ ጋር ብንጠቀም ኖሮ ውጤቱ ሌላ ይሆን ነበር፡፡ እንዳያችሁት የገባው ግብ በእንቅስቃሴ አይደለም ከቆመ ኳስ ነው፡፡ በሁለታችንም በኩል የነበረው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው፡፡ 

ከአመቱ መጀመሪያ ጀምሮ በተለይ በመጀመሪያው ዙር በተደጋጋሚ ይታይ የነበረ ክፍተት የአጨራረስ ድክመታችን ነው፡፡ በተወሰነ ደረጃ የግብ እድሎችን ፈጥረን አለመጠቀሙ በቡድኑ ውስጥ ያለ ችግር ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ምንም ማድረግ አይቻልም ባሉን ልጆች በቀሪ ጨዋታዎች ላይ የተገኙ እድሎችን ለመጠቀም ስራ ሰርተን ውጤት ይዘን ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን፡፡ 

የፋሲል ከተማ አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ

ጨዋታው ጥሩ ነው፡፡ አንድ የኤሌክትሪክን ጨዋታ ከዚህ በፊት አይቼ ነበር እና እነሱ ኳስ መቆጣጠር ይፈልጋሉ ግን የተሳካ የኳስ ቁጥጥር አልነበረም የሚጠቀሙት፡፡ እኛ ግን በመልሶ ማጥቃት ቶሎ ቶሎ ኳሱን አፍጥነን ለመጫወት ሞክረናል፡፡ ያው በሜዳው የተሻለው ቡድን ሶስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል ብዬ አስባለው፡፡ ወደ ግብ የምንሄድበት መንገድ ከእነሱ የተሻለወደ ግን እንቀርብ ነበር፡፡ ምንአልባት ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ውጤትን አስጠብቀን ለመውጣት ስንል የተወሰኑ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ እንደአጠቃላይ ግን ወደ ግብ የምንሄድበት መንገድ እኛ የተሻልን ነበርን ብዬ ነው ማስበው፡፡ 

በተወሰነ ስኳድ ነው እስካሁን የምንጫወተው፡፡ ተመሳሳይ ችግር አለብን፡፡ ነገር ግን ልጆቻችን ጉልበት ይፈልጉ ነበር፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የልምድ ችግሮች ነበሩብን፡፡ አይታችሁ እንደሆነ ግብ ጠባቂው ኳስ ይዞ ሰዓት መግደል ይፈልጋል፡፡ ይህ የልምድ ማጣት ችግሮች ናቸው፡፡ አሁን ግን ተመልሰን ወደ ውድድሩ ገብተናል ብለን ነው የምናስበው፡፡

መከላከያን ስንገጥም 2-1 እየመራን ባለቁ ደቂቃዎች ላይ ማጥቃትን ነበር ቡድናችን የሚፈልገው፡፡ እንደዛ በማድረጋችን ቡዙ ነገር አጥተናል፡፡ ስለዚህ ያገኘናትን ውጤት ለማስጠበቅ ስንል ወደ መጨረሻ አከባቢ ጫናዎች ነበሩብን፡፡ ይህ ደግሞ ምንአልባትም ከልምድ ነው፡፡ ለሊጉም አዲስ ነን ከልምድ አንፃር ነው፡፡ ጨዋታውን ለማሸነፍ የነበሩ ፍላጎቶች ግን የእኛ የተሻለ ነበር፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *