የጨዋታ ሪፖርት | ወልድያ 1-0 ወላይታ ድቻ

የኢትዮጰያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዛሬው እለት በተደረጉ 6 ጨዋታዎች ሲጀመሩ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታድየም ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ወልድያ 1-0 በማሸነፍ በሜዳው ነጥብ መሰብሰቡን ቀጥሏል፡፡

ጨዋታውን ለመመልከት በርካታ የወልድያ ደጋፊዎች ወደ ወልድያ መጓዛቸውን ተከትሎ ሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታድየም በሁለቱ ደጋፊዎች ህብረ ዜማ ደመቅ ብሎ ታይቷል፡፡

ከተያዘለት ሰአት 10 ደቂቃ ያህል ዘግይቶ የተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም የወላይታ ድቻ የኳስ ቁጥጥር እና የጎል ሙከራ ብልጫ ታይቶበታል። ድቻ በጨዋታው የመጀመርያውን ሙከራ ያደረገ ሲሆን በ10ኛው ደቂቃ ተመስገን ዱባ የሞከረውን አደገኛ ኳስ ለቡድኑ ወሳኙነቱን ያስመሰከው እና በወልድያ በኩል የጨዋታው ኮከብ የነበረው ኤሚክሪል ቢሌንጌ አድኖታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አንዱአለም ንጉሴ እና ያሬድ ብርሀኑ በማራኪ አንድ ሁለት ቅብብል አልፈው ለያሬድ ሀሰን የተመቻቸውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ያሬድ አስቆጠረው ሲባል ያመከነው ኳስ በወልድያ በኩል የመጀመሪያው አጋማሽ ለጎል የቀረበ ሙከራ ነበር። በ24 ደቂቃ በመስመር ተቀባብለው የገቡት ድቻዎች ከሳጥኑ ውስጥ አክርረው የመቱትን ኳስ አሁን በድጋሚ ቢሌንጌ በጥሩ ሁኔታ አድኖታል።

የመጀመርያው አጋማሽ ከተጋመሰ በኋላ በ33ኛው ደቂቃ የዳኛን ውሳኔ በመቃወም የድቻ ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከዳኞች ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ለ3 ደቂቃ ያህል የተቋረጠ ቢሆንም በድቻ የቅጣት ምት እንደገና ጨዋታው ጀምሯል። ከዚህ በኋላ ባሉት ቀሪ የመጀመርያው አጋማሽ ደቂቃዎች ሙከራዎች ያልተስናገዱ ሲሆን በ45ኛው ደቂቃ አንዱአለም ንጉሴ አንድ ተጫዋች አታሎ የመታው ኳስ ኢላማውን ከሳተበት ውጪ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ወልድያ መሻሻል ቢያሳይም ግልፅ የግብ እድል ለመፈጠር ሲቸገር ተስተውሏል። በአብዛኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የቡድኑ ግብ አዳኝ የሆነው አንዱአለም ንጉሴ ለብቻው ተነጥሎ በድቻ የግብ ክልል ውስጥ ተውጦ የዋለ ሲሆን የሚያገኛቸውም ኳሶች አጋዥ በማጣት ሲባክኑ ተስተውሏል።

በአንጻሩ ወላይታ ድቻ ከወልድያ በተሻለ የግብ እድሎች መፍጠር ችለው የነበረ ሲሆን በ53ኛው ደቂቃ ከግብ ክልሉ አቅራቢያ ያገኙትን ቅጣት ምት በዛብህ መለዮ በጥሩ ሁኔታ ሞክሮ ቢሌንጌ ያዳነበት እንዲሁም በ71ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል ወደ ሳጥን የተላከችውን ኳስ ዳግመም በቀለ ሞክሮ ቢሌንጌ የያዘበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ጨዋታው በዚህ ሒደት ቀጥሎ በ85 ደቂቃ ጫላ ድሪባ ያመቻቸውን ኳስ ተጠቅሞ ተቀይሮ የገባው አማካዩ ሐብታሙ ሸዋለም ወደ ግብነት ቀይሯት ወልድያን መሪ አድርጓል፡፡ በዚህ አመት አማራ ውሀ ስራን ለቆ ወልድያን የተቀላቀለው የአማካዩ በሰማያዊ እና ነጩ መለያ የመጀመሪያ ግቡን አስቆጥሯል፡፡

ከጎሉ በኃላ መነቃቃት የታየባቸው ወልድያዎች በተደጋጋሚ ወደ ድቻ የግብ ክልል ቢደርሱም ይህ ነው የሚባል አደጋ የሚፈጥር ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው በወልድያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው በሁለቱም ደጋፊዎች በኩል ጥሩ የሚባል ስፖርታዊ ጨዋነት የተስተዋለ ሲሆን ከጨዋታው ፍጻሜ በኋላ ማልያ የተቀያየሩ ደጋፊዎችንም ማስተዋል ችለናል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ወልድያ ነጥቡን 30 በማድረስ በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ሲደላደል በከፍተኛ የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በ23 ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ለመቆየት ተገዷል፡፡

Leave a Reply