የጨዋታ ሪፖርት | አርባምንጭ ከተማ 0-2 ድሬዳዋ ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት መርሀ ግብር ወደ አርባምንጭ ያመራው ድሬዳዋ ከተማ አርባምንጭ ከተማን 2-0 በመርታት ከወራጅ ቀጠናው የሚያርቀው ነጥብ መሰብሰቡን ቀጥሏል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት አሳይተዋል፡፡ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎችም በሀብታሙ ወልዴ እና በረከት ይስሃቅ አማካይነት አስደንጋጭ የግብ ሙከራ ማድረግ ችለዋል፡፡

በ16ኛው ደቂቃ በጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ያሳየው ዮሴፍ ዳመሙዬ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ በመምታት በጃክሰን ፊጣ መረብ ላይ አሳርፎ ድሬዳዋን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ዮሴፍ ከኢትዮጵያ ቡና በውሰት ወደ ድሬዳዋ ካመራ ወዲህ በብርቱካናማው ማልያ የመጀመርያ ጎሉ ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽም ድሬዳዋ ከተማ የበላይነቱን በማሳየት የአርባምንጭን የግብ ክልል በተደጋጋሚ መፈተሽ የቻለ ሲሆን አርባምንጭ በአንፃሩ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በተለይ ለወትሮው የቡድኑ ጠንካራ ጎን የነበረው የአማካይ ክፍል ተዳክሞ መቅረብ የድሬዳዋ ተጫዋቾች እንደልብ እንዲንቀሳቀሱ አስችሏቸዋል፡፡

ጨዋታው በድሬዳዋ የበላይነት ቀጥሎ በ83ኛው ደቂቃ  በረከት ይስሃቅ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን በመግባት የአርባምንጭ ተከላካዮች እና የግብ ጠባቂውን ጃክሰን ፊጣ ስህተት በመጠቀም ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ በድሬዳዋ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው በኃላም የአርባምንጭ ከተማ ደጋፊዎች አሰልጣኝ ጳውሎስ ፀጋዬ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ ተስተውሏል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ ባስመዘገበው ጣፋጭ የሜዳ ውጪ ድል ነጥቡን 28 በማድረስ ከወራጅ ቀጠናው በ5 ነጥቦች መራቅ ሲችል በሁለተኛው ዙር ብቻ በሜዳው ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ 29 ነጥብ ላይ ረግቷል፡፡

Leave a Reply