ጋቦን በሶስት ከተሞች ከግንቦት 6 ጀምሮ በምታስተናግደወ የ2017 ቶታል የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ኢትዮጵያ ተሳታፊ እንደምትሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን አስታውቋል፡፡ ማሊ በአለማቀፉ የእግርኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) እገዳ መጣሉን ተከትሎ ነው ቀይ ቀበሮዎቹ ተሳታፊ የመሆን እድል ያገኙት፡፡
ኢትዮጵያ በመጨረሻ ዙር ማጣሪያ በማሊ የ4-1 አጠቃላይ ውጤት ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ ብትሆንም በመጋቢት ወር ፊፋ ማሊን ከማንኛውም የኢንተርናሽናል እግርኳስ ማገዱን ተከትሎ የመሳተፍ እድሉን አግኝታለች፡፡ ካፍ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ውድድሩን በተመለከተ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ረቡዕ እለት የተሰበሰበው የስራ አስፈፃሚ ኮሜቴው በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ውሳኔን አሳልፏል፡፡ በዚህም በአሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ የሚመራው ቡድኑ በአዳማ ወይም ሀዋሳ ላይ ከሰኞ ጀምሮ ከትሞ ልምምዱን እንደሚጀምር ታውቋል፡፡ አሰልጣኝ አጥናፉ ከዚህ ቀደም የነበረውን ቡድን እና ከ17 ዓመታ በታች ሊግ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች አዲስ ተጫዋቾች ይዘው ዝግጅት እንደሚጀምሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የማሊ የስፖርት ሚኒስቴር የሃገሪቱን የእግርኳስ ፌድሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባላትን ማባረሩን ተከትሎ ፊፋ በመንግስት ጣልቃ ገብነት የምዕራብ አፍሪካዋን ሃገር ከኢንተርናሽናል ጨዋታዎች አግዷል፡፡ የእገዳው የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የሆኑን በአፍሪካ ክለቦች ውድድር ተሳታፊ የነበሩት ጆሊባ እና ኦንዜ ክሬቸርስ ነበሩ፡፡ ሁለቱ የባማኮ ክለቦች በእገዳው ምክንያት ከካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ በፎርፎ ተሸንፈው ተሰናብተዋል፡፡ አሁን ደግሞ ሊጀመር ከወር ያነሰ ግዜ በቀረው የ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የነበረው የ17 ዓመት ብሄራዊ ቡድኗ የቅጣቱ ሰለባ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ ማሊን ተክታ በምድብ ሁለት ከታንዛኒያ፣ አንጎላ እና ኒጀር ጋር ስትመደብ በምድብ አንድ አዘጋጇ ጋቦን፣ ጊኒ፣ ካሜሮን እና ጋና ተደልድለዋል፡፡ ቀይ ቀበሮዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ግንቦት 7 ከታንዛኒያ ጋር በፖር ዠንቲል ሲያደርጉ ግንቦት 10 ላይ ኒጀርን ይገጥማሉ፡፡ የመጨረሻ ጨዋታቸው ከአንጎላ ጋር ፍራንስቪል ላይ ይሆናል፡፡
የ17 ዓመት በታች ዋንጫን በቅድሚያ የማስተናገድ ቅድሚያ የተሰጣት ማዳጋስካር ናዘጋጀት አለመቻሏን ተከትሎ ጋቦን ሃላፊነቱን ተረክባለች፡፡ ጋቦን የታዳጊዎች ውድድሩን በሊበርቪል፣ ፍራንስቪል እና ፖር ዠንቲል ባሉ ሶስት ስታዲየሞች ታስተናግዳለች፡፡
በ1997 እ.ኤ.አ ቦታስዋና ባሰናዳችው የአፍሪካ ታዳጊዎች ዋንጫ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ አራተኛ መውጣቷ ይታወሳል፡፡ ከ1997 ወዲህ በታዳጊዎች ውድድር የመሳተፍ እድል ስታገኝ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡