የጨዋታ ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ 3-2 ሲዳማ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት የወንድማማቾች ደርቢ በሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና መካከል ተካሂዶ በተመጣጣኝ ፉክክር እና የድንጋይ እሩምታ ታጅቦ በሀዋሳ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከሌላው ጊዜ በተለየ ከቀትር ጀምሮ የስታድየሙ ወንበሮች በደጋፊዎቻቸው ተሞልቶ እጅግ ማራኪ በሆነ ዝማሬ ታጅቦ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ  15 ደቂቃዎች ፋተታ የማይሰጥ እንቅስቃሴ ያደረገው ሀዋሳ ከተማ ገና በሁለተኛው ደቂቃ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ሲዳማ የግብ ክልል በማምራት ዮሀንስ ሱጌቦ ያሻማትን ኳስ ጃኮ አራፋት ከመረብ አዋህዶ መሪ መሆን ችለዋል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኋላም ሀዋሳ ከተማወች ጫና ፈጥረው በመጫወት ከአራት ደቂቃ በኃላ በግራ መስመር ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ጋዲሳ መብራቴ ያሻገረለትን ኳስ ፍሬው ሰለሞን በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ሀዋሳ ከተማ በሁለት ግብ ልዩነት እንዲመራ አስችሎታል፡፡

በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በተቆጠሩ ጎሎች 2-0 የተመሩት ሲዳማ ቡናዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተደጋጋሚ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ ፈጣኑ አጥቂ አዲስ ግደይ በተለይ ሰንደይ ሙቱኩ በረጅሙ የሰጠውን ኳስ መትቶ አዲስአለም ተስፋዬ ያወጣበት ተጠቃሽ ሙከራ ነበር፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ትርታዬ ደመቀ በግንባሩ በመግጨት ሞክሮ ለጥቂት ወደ ላይ የወጣበትም በሲዳማ ቡና በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነበር፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ አፀያፊ ስድቦች እና ረብሻ ከማስተናገዱ ባሻገር በሽኩቻዎች ፣ በርካታ ቢጫ ካርዶች እና ሶስት ግቦች ታጅቦ የደርቢ መልክን ያሳየ ሆኖ ታይቷል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ ሁለት ግብ የተቆጠረባቸው ሲዳማዎች ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማደድረጋቸውን በመቀጠል በ56ኛው ደቂቃ ግሩም አሰፋ በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ በሚገባ የተቆጣጠረው አዲስ ግደይ አስቆጥሮ ቡናዎችን ወደ ጨዋታ ሪትም እንዲገቡ አስችሏል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት ሲዳማ ቡናዎች በተለይም ወሰኑ ማዜን ቀይረው ካስገቡ በኋላ በመስመር በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረሳቸው ምክንያት ሲሆን ታይቷል፡፡ በ80ኛው ደቂቃ ላይም ጥረታቸው ሰምሮ አማካዩ ሙሉአለም መስፍን ከመስመር በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ የሶሆሆ ሜንሳሀህን ቅጣተት ተከትሎ በመጀመርያ አሰላለፍ የተካተተው ግብ ጠባቂው አላዛር መርኔን ስህተት ተጠቅሞ አዲስ ግደይ ሲዳማን አቻ የምታደርግ ግብ አስቆጥሯል፡፡

ከ2-0 መሪነት አቻ የሆኑት ሀዋሳ ከተማዎች ወደ መሪነታቸው ለመመለስ የፈጀባቸው ሁለት ደቀማ ብቻ ነበር፡፡ በ82ኛው ደቂቃ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የተገኘውን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን  ግብ ጠባቂው ለአለም ብርሀኑን አልፎ ሀዋሳን መሪ አድርጓል፡፡ ከግቧ በኃላ በትሪቡን ከሚገኙ ደጋፊዎች በተወረወረ የድንጋይ ናዳ ምክንያት ጨዋታው ለ8 ደቂቃዎች የተቋረጠ ሲሆን  የሀዋሳ ከተማው ምክትል አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት መጠነኛ ጉዳት አጋጥሞታል፡፡

የጨዋታውን መንፈስ የቀየረው ክስተት ጋብ ካለ በኋላ ከተቋረጠበት ሲቀጥል ሀዋሳ ከተማዎች ተከላክለው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ፤ ሲዳማ ቡናም ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ ሆኖም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው ከሲዳማ ቡና በኩል አዲስ ግደይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በሀዋሳ ከተማ በኩል ግብ የሚሆኑ አጋጣሚወችን ሲያመክን የነበረው አዲስአለም ተስፋዬ በሰላም ውሀ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የ5000 ብር ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና የሊጉን መሪነት የመያዝ እድሉን ሲያመክን ሀዋሳ ከተማ በሁለተኛው ዙር እየያሳየ ባለው መሻሻል ቀጥሎ ነጥቡን 31 በማድረስ 7ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡

ያጋሩ

Leave a Reply