የጨዋታ ሪፖርት | ጅማ አባ ቡና 1-1 አዳማ ከተማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት 6 ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች ሲደረጉ ጅማ ላይ አዳማ ከተማን ያስተናገደው ጅማ አባ ቡና በ87ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ነጥብ ተጋርቶ ሊወጣ ችሏል።

በሊጉ ኦሮሚያ ክልልን በሚወክሉት ሁለቱ ክለቦች መካከል በተደረገው ጨዋታ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት አዳማ ከተማ ወደ ሊጉ መሪዎች ይበልጥ መጠጋት እንዲችል ፤ ጅማ አባ ቡና ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ራቅ ብሎ እንዲቀመጥ የሚያስችል የነበረ እንደመሆኑ ውጥረት የሰፈነበት ጨዋታ እንድናይ አድርጎናል።

ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ የጅማ አባ ቡና እግርኳስ ክለብ ለአዳማ ከተማ ያዘጋጀውን የማስታወሻ ስጦታ በዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሃኪም አማካኝነት አበርክቷል።

በጨዋታው አዳማ ከተማ በ4-3-3 ቅርፅ የመስመር አጥቂዎቹ ዳዋ ሁቴሳ እና ቡልቻ ሹራ ለሚካኤል ጆርጅ ኳሶችን በማሻገር እና ፍጥነታቸውን ተጠቅመው ወደ ግብ በመድረስ ዕድሎችን እንዲፈጥሩ ለማድረግ ሲሞክሩ ጅማ አባ ቡናዎች እንደተለመደው በ4-2-3-1 አሰላለፍ ዳዊት ተፈራን ከፊት አጥቂው መሀመድ ናስር ጀርባ በመጠቀም አሜ መሀመድ እና ኪዳኔ አሰፋ ከመስመር የማጥቃት እንቅስቃሴውን እንዲቀላቀሉ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።

ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አንስቶ አዳማ ከተማዎች በተለይ በዳዋ ሁቴሳ አማካኝነት የጅማ አባ ቡናን የተከላካይ መስመር ለመፈተን የሞከሩ ሲሆን የጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ አጋጣሚም በ5ኛው ደቂቃ ለዳዋ በአየር የተላከ ኳስ አጥቂውን ከጀማል ጣሰው ጋር አገናኝቶት የቀኝ ተከላካዩ ጀሚል ያቆብ ከኋላ መጥቶ ያቋረጠው ኳስ ነበር። በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የዋለው ዳዋ ሁቴሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላም ወደግብ ከርቀት የሞከረው ኳስ በጀማል ተመልሶበታል።

የግብ አጋጣሚዎቹን በመፍጠሩ ረገድ በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫውን ወስደው የነበሩት አዳማ ከተማዎች በ21ኛው ደቂቃም በቡልቻ ሹራ አማካኝነት ጥሩ የግብ ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በ28ኛው ደቂቃ ዳዋ ሁቴሳ የጅማ አባ ቡናው አማካይ ሄኖክ ካሳሁን በሰራው ስህተት ምክኒያት ያገኘውን ኳስ ከርቀት ወደግብ ቢሞክርም ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ወጥቶበታል።

ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎች ሲያደርጉ የነበሩት አዳማዎች በመጨረሻም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ መሪ የሚያደርጋቸውን ግብ በ34ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችለዋል። ሞገስ ታደሰ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ዳዋ ሁቴሳ የግብ ጠባቂው ጀማል የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጠቅሞ ከመረብ አሳርፏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ጅማ አባ ቡናዎች የአዳማው ግብ ጠባቂ ጃኮ ፔንዜ ወደግብ የተሻገሩ ኳሶችን በአግባቡ ለመቆጣጠር ባለመቻሉ ምክኒያት ሁለት የግብ አጋጣሚዎችን ማግኘት ቢችሉም መጠቀም አልቻሉም ነበር። አሰልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌም በአዳማ ከተማዎች የአካል ብቃት ብልጫ ምክኒያት የተለመደውን እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻለውን ፈጣሪ አማካይ ዳዊት ተፈራ አስወጥተው በ5 ቢጫ ምክኒያት ከቅጣት የተመለሰውን ዩጋንዳዊ ኪሪዜስቶም ንታምቢ በማስገባት የጅማ አባ ቡናን አጨዋወት የቀየረ የተጫዋች ለውጥ አድርገዋል። በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ቡልቻ ሹራ ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰውን ካለፈ በኋላ ኳስን መቆጣጠር አቅቶት ያባከነው አጋጣሚ በአዳማ በኩል የሚጠቀስ ሌላ ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ ለማግኘት ተጭነው መጫወት የጀመሩት አባ ቡናዎች ከተጋጣሚያቸው የተሻለ እንቅስቃሴን ማሳየት ችለዋል። መሀመድ ናስር ለሁለት ግልፅ የግብ ዕድሎችን አግኝቶ ወደግብ የመሞከር ወይም ለቡድን አጋሩ የማቀበል ውሳኔን ቶሎ መወሰን ባለመቻሉ የባከኑት አጋጣሚዎች ለአባ ቡና የሚያስቆጩ ነበሩ፤ ዩጋንዳዊው ኪሪዜስቶም ንታምቢም ከረጅም ርቀት በመምታት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርጓል። በተቃራኒው ጎል ሚካኤል ጆርጅ እና ሱራፌል ዳኛቸው ያደረጓቸውን ሙከራዎች ጀማል ጣሰው በቀላሉ አድኗል።

ከጨዋታው 70ኛ ደቂቃ ጀምሮ በሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች መሀል በተፈጠሩ አለመግባባቶች ምክኒያት አንዳንድ ተጫዋቾች ለጥል ሲጋበዙ ተስተውሏል። ጨዋታውን የመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማም ጨዋታውን ለመቆጣጠር የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ለመምዘዝ ተገደዋል።

የጨዋታው መደበኛ ክፍለጊዜ ሊጠናቀቅ 3 ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩ ጅማ አባ ቡናዎች አቻ ለመሆን ችለዋል። በመሀመድ ናስርን ተክቶ የገባው በድሉ መርዕድ በኪዳኔ አሰፋ ተሞክሮ ጃኮ ፔንዜ የተፋውን ኳስ ከቅርብ ርቀት አግኝቶ ስታዲየሙን የሞላውን ደጋፊ ጮቤ ያስረገጠች ግብ አስቆጥሯል።

በጨዋታው ቀሪ ደቂቃዎች ዒላማቸውን ያልጠበቁ ከርቀት የተመቱ ኳሶች ውጪ ሙከራዎች ሳይደረጉ ጨዋታው 1 – 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ ነጥቡን  36 አድርሶ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ሲል 24 ነጥቦችን የሰበሰበው ጅማ አባ ቡና መከላከያን በልጦ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

Leave a Reply