የጨዋታ ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 0-0 ደደቢት

በ23ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የገጠመው ደደቢት ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ንግድ ባንክ አርባምንጭ ከሜዳው ውጪ መርታቱን ተከትሎ በጨዋታው ላይ መነቃቃቶች ሲያሳይ አዲስ አበባ ከተማን በአምስት ደቂቃዎች ውስጥ በተቆጠሩ ሶስት ግቦች የረታው ደደቢት በግብ ሙከራ ተሽሎ ታይቷል፡፡

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ 20ኛው የምስረታ ዓመቱን እያከበረ የሚገኘው ደደቢት እግርኳስ ክለብ መስራች ለነበሩት ኮሎኔል አውል አብዱራሂም ሽልማት ተበርክቷል፡፡

 

በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ወደ ግብ በመቅርብ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ደደቢቶች ናቸው፡፡ አስራት መገርሳ እና ሮበን ኦባማ የንግድ ባንኩን ግብ ጠባቂ ኤማኑኤል ፌቮን መፈተን ሲችሉ የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ በ19ኛው ደቂቃ የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ ማራኪ የኳስ ፍሰት በጨዋታው ላይ ባይታይም ንግድ ባንኮች በተደጋጋሚ በፈጣን እንቅስቃሴ ተጋጣሚያቸውን ለመረበሽ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ለዚህም ማሳያ በ26ኛው ደቂቃ ቢኒያም በላይ የደደቢት ተከላካዮች አታሎ ካለፈ በኃላ ወደ አደጋ ክልሉ ያሻገረውን ኳስ የሚጠቀምበት የንግድ ባንክ ተጫዋች ታጣ እንጂ ሃምራዊዎቹ ቀዳሚ ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ጨዋታው እስከመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ድረስ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የጠራ የግብ እድሎች ሲፈጠሩ አልተመለከትንም፡፡

ከእረፍት መልስ ደደቢት ግብ አስቆጥሮ ወደ ለሊጉ ዋንጫ የሚያደርገውን ፉክክር ለማጠናከር የሚችልባቸውን እድሎች አምክኗል፡፡ በተለይ በሁለተኛው 45 ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የዳዊት ፍቃዱን እና የጌታነህን ጠንካራ ሙከራዎች ፌቮ በድንቅ ሁኔታ አምክኗቸዋል፡፡ በ77ኛው ደቂቃ የንግድ ባንኩ ፍቃሱ ደነቀ ከመስመር ላይ ኳስ በማውጣት ሰማያዊዎቹ መሪ መሆን የሚችሉበት ግብ አምክኗል፡፡ በተቃናኒው ናይጄሪያዊው ፒተር ንዋድኬ በደደቢት የግብ ክልል ከቢኒያም የተቀበለው ሁለት ጥሩ ኳሶች ሳይጠቀምባቸው ቀርተዋል፡፡ ጨዋታው ሊገባደድ ሰባት ደቂቃዎች ሲቀሩት ፒተር መሬት ለመሬት የመታውን ኳሽ ክሌመንት አዞንቶ በቅልጥፍና ግብ ከመሆን ታድጓል፡፡ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃወች ደደቢቶች ጫና ፈጥረው ወደ ፊት በሚላኩ ኳሶች ለመጠቀም ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው አቻ ለመለያየት ተገደዋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ደደቢት በ40 ነጥብ የሊጉ መሪ መሆን ሲችል ላለመውረድ በመታገል ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ20 ነጥብ ባለበት 15ኛ ደረጃ ረግቷል፡፡

 

የአሰልጣኞች አስተያየት

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ

“እኛ ያለንበት ዞን አደገኛ ዞን ነው፡፡ ከባለፈው ሳምንት በነበረው ሂደት ላይ ቡድኑ አቻ በመውጣት እና በመሸነፍ ሂደት ውስጥ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ልጆቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የስነ-ልቦና ጫና ይፈጥርባቸው ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት አርባምንጭ ላይ ያገኘነው ነጥብ ሲደመር ደግሞ ያሉብንን ስህተቶች ብዙ አርመናል፡፡ እንደሚታየው አምስት እና አራት የሚሆኑ አዲስ ተጫዋቾችን በሁለተኛው ዙር ያስገባነው፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች ቡድኑን በደንብ እስኪዋህዱ ድረስ አንዳንድ የምናያቸው ችግሮች ነበሩ፡፡ አሁን ቡድኑ የተሻለ ለውጥ አለው ብዬ አስባለው፡፡”

“እያንዳንዱ ጨዋታ ለእኛ አስፈላጊ ነው፡፡ ለእኛ የሚያስፈልገን ሶስት ነጥብ ነው፡፡ ሜዳ ውስጥ የምንገባው ሁሌም ሶስት ነጥብ ለማግኘት ነው፡፡ ጨዋታው የሰጠንን ነገር ደግሞ ተቀብለን ቀጣይ ጨዋታዎች ላይ አሸንፈን ለመውጣት ጥረት እናደርጋለን፡፡ ሁሉም ጨዋታዎች ለእኛ ወሳኝ ናቸው፡፡ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ወደ አሸናፊነት መመለስ አለብን፡፡ ያሉት ተጋጣሚዎቻችን እንደሚታወቀው ለቻምፒዮንነት የሚሄዱ ናቸው፡፡ እነሱም ለማሸነፍ ነው የሚሄዱት፡፡ ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ ነው የሚጫወቱት፡፡ ደደቢት አራቱንም ተከላካዮች ከመስመር ወጥተው ለመጫወት አልሞከሩም፡፡ እኛ ግብ ልናገባ የምንችልባቸው እድሎች በሙሉ ቆመው በመከላከል አባክነዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ ጨዋታው የተሻለ ነበር፡፡”

 

የደደቢት ምክትል አሰልጣኝ ኤልያስ ኢብራሂም

“ሙሉ በሙሉ ለዋንጫ እንደመፎካከራችን ያለንን ሃይል ተጠቅመን በማጥቃት ላይ የተመረኮዘ እንቅስቃሴ ይዘን ነው የገባነው፡፡ ወደፊት ተጭነን ሙከራዎችን አድርገናል፡፡ ያገኘናቸውን እድሎች አምክነን ይህንን ውጤት ይዘን ልንወጣ ችለናል፡፡”

“ተጭነን ወደ ፊት ለመጫወት ነው የሞከርነው፡፡ ወራጅ ቀጠናው ውስጥ ያለ ቡድን (ንግድ ባንክ) እንደመሆኑ ሙሉ በሙሉ አጥቅተን ለመጫወት ነው የሞከርነው፡፡ ልጆቻችን የተቻላቸውን አድርገው ነው የወጡት ማለት እችላለው፡፡ እነሱ በመከላከሉ ላይ ትኩረት አድርገው ሲጫወቱ ስለነበረ የማጥቃት ሃይላችንን ለመጨመር ያህል ነው ሽመክት ወደ ውስጥ ገብቶ እንዲጫወት ያደርግነው፡፡ያሉንን ጥሩ ጎኖች አዳብረን መጥፎ ጎናችንን ደግሞ አስተካክለን ከዚህ የተሻለ ውጤት እና ደረጃ ላይ መጨረስ ነው ዋና አላማችን፡፡”

Leave a Reply