የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሀሙስ በአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች ሲደረጉ ጅማ ላይ ጅማ ከተማ ናሽናል ሲሚንትን አስተናግዶ 5-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የምድብ ለ መሪነቱን ማጠናከር የቻለበትን ውጤት አስመዝግቧል። አጥቂው አቅሊስያስን በጉዳት ላላሰለፈው ጅማ ከተማ ግቦቹን ቡድኑ ያለውን የስብስብ ጥልቀት እና ሰፊ የማጥቃት አማራጭ በጠቆመ መልኩ ሶስት የተለያዩ ተጫዋቾች ሲያስቆጥሩ አጥቂው ተመስገን ገብረኪዳን ሶስት ግቦችን ከመረብ አሳርፎ ሃትሪክ ሰርቷል።
ተቀራራቢ የሆነ ፉክክር በተስተዋለበት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ተመስገን ገ/ኪዳን ከሮቤል አስራት የተሻገረለትን ኳስ በመጠቀም ጅማ ከተማን መሪ አድርጓል። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ፈርሃን ሰዒድ ናሽናል ሲሜንትን አቻ ያደረገ ግብ ቢያስቆጥርም በ32ኛው ደቂቃ ተመሰገን ገ/ኪዳን ከ25 ሜትር አካባቢ ወደግብ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሮ ጅማ ከተማን ወደ መሪነቱ መልሷል። በ35ኛው ደቂቃ ይድነቃቸው ብርሃኑ በቀጥታ ወደግብ የመታው ቅጣት ምት ግብ ጠባቂው ሚኪያስ ጌቱ ሲያድነው የተመለሰውን ኳስ ፈርሃን ሰዒድ አግኝቶ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር ናሽናል ሲሚንትን ዳግም አቻ አድርጓል። በ45ኛው ደቂቃ ከኤልያስ አታሮ ከግራ መስመር ያሻገረው ኳስ በአደጋ ክልሉ ውስጥ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ተመሰገን ገ/ኪዳን አስቆጥሮ ቡድኑ በመሪነት ለእረፍት እንዲወጣ አስችሏል።
በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ናሽናል ሲሚንቶች ውጤቱን ለማጥበብ ወደፊት ገፍተው ሲጫወቱ ጅማ ከተማዎች በአንፃሩ በተለይ አብዱልከሪም አባፎጊ ተቀይሮ ከገባ በኋላ ውጤቱን ለማስጠበቅ በመከላከል እና በሚፈጠሩ ክፍተቶች ተጠቅመው በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። በጨዋታው 78ኛ ደቂቃም በመልሶ ማጥቃት የሄደውን ኳስ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኤልያስ አታሮ አስቆጥሮ መሪነቱን ማስፋት ችሏል። ከ10 ደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ አካሄድ ከግራ መስመር በኩል የተሻገረውን ኳስ ሔኖክ መሃሪ የጅማ ከተማ አምስተኛ እና የማሳረጊያ ግብ አድርጎታል።
በሌሎች ጨዋታዎች ወልቂጤ ከተማ ዲላ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ ያደረገ ሲሆን ቦንጋ ላይ ከከፋ ቡና ጋር የተጫወተው ሀላባ ከተማ 2-2 ተለያይቷል። ወራቤ ላይ የተደረገው የስልጤ ወራቤ እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ በፀጥታ ችግር ምክኒያት በተደጋጋሚ ከተቆራረጠ በኋላ በስልጤ ወራቤ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ሻሸመኔ ከተማ ነቀምት ከተማን 2-1 በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥቦችን መያዝ ሲችል አርሲ ነገሌ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት በጅንካ ከተማ 0-2 በሆነ ውጤት ተሸንፏል። ድሬዳዋ ላይ ሁለት የፖሊስ ክለቦችን ባገናኘው ጨዋታ ድሬዳዋ ፖሊስ በፌደራል ፖሊስ ላይ የ3-1 ድል ተቀዳጅቷል። በሌላ የምድቡ ጨዋታ ደቡብ ፖሊስ ሀዋሳ ላይ ነገሌ ቦረናን 2-0 አሸንፏል።
ምድቡን ጅማ ከተማ በ33 ነጥቦች ሲመራ ወልቂጤ ከተማ በ30 ነጥብ ይከተላል። ሀላባ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና በ29 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ደረጃውን ባያሻሽልም ከመሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ የቻለው ሻሸመኔ ከተማ በ28 ነጥቦች 5ኛ ነው።
የምድቡ መሪ የሆነው ጅማ ከተማ ሶከር ኢትዮጵያ ስለ ጨዋታው እና ተያያዥ ጉዳዮች ለመስራት ወደ ጅማ ባመራችበት ወቅት በክለቡ ለተደረገላት አቀባበል እና መስተንግዶ ከፍ ያለ ምስጋና ታቀርባለች፡፡