ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ – የባህርዳር ደርቢ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ መሪዎቹ ማሸነፍ አልቻሉም

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሀሙስ ሲደረጉ የምድቡ መሪዎች ነጥብ ጥለዋል።

ከተደረጉት 8 ጨዋታዎች ውስጥ 3ቱ ያለምንም ግብ ሲጠናቀቁ በሳምንቱ በተደረጉ ጨዋታዎች 8 ግቦች ብቻ ተስተናግደዋል። ከሜዳው ውጪ ሰበታ ከተማን የገጠመው የምድቡ መሪ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያለግብ አቻ ተለያይቷል። በሌላ ተጠባቂ ጨዋታ ከወልዋሎ በአንድ ነጥብ አንሶ የሚገኘው መቀለ ከተማ አዲግራት ላይ ከሽሬ እንዳስላሴ ጋር በተመሳሳይ 0-0 በሆነ ውጤት ጨዋታውን አጠናቋል። በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው አራዳ ክፍለከተማ ቡራዩ ከተማን ያስተናገደበት ጨዋታ ሌላው ያለግብ የተጠናቀቀ ጨዋታ ነበር።

አማራ ውሀ ስራ እና ባህርዳር ከተማ ያደረጉት ተጠባቂ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ተስተውሎበት በ 1-1 ውጤት ተጠናቋል። በዚህ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ መሪ የሆነበትን ግብ በ68ኛው ደቂቃ በኤርምያስ ዳንኤል አማካይነት ቢያስቆጥርም አማራ ውሃ ስራ በ87ኛ ደቂቃ በእዮብ ወ/ማርያም አማካይነት አቻ መሆን ችሏል።

በሌሎች ጨዋታዎች ሱሉልታ ከተማ አዲስ አባባ ፖሊስን ከሜዳው ውጪ 1-2 ሲያሸንፍ  ለገጣፎ ለገዳዲ ኢትዮጵያ መድህንን አክሱም ከተማ ወሎ ኮምቦልቻን በተመሳሳይ 1-0 ውጤት አሽንፈዋል:: በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ኢትዮጵያ ውሀ ስፖርትን አስተናግዶ 1-0 ተሸንፏል።

ውጤቶቹ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ለውጥ ያላስከተሉ ሲሆን ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ በ37 ነጥብ በመሪነቱ ቀጥሏል። መቀለ ከተማ በ36፣ ባህርዳር ከተማ በ30፣ ሽረ እንዳስላሴ በ28 ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል።

Leave a Reply