በሁለተኛው ዙር ውጤት አልባ ጉዞ እያደረገ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጸጋዬን ከሀላፊነት ማንሳቱ ታውቋል፡፡
የአርባምንጭ ከተማ ቦርድ በክለቡ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ ስብሰባ የተቀመጠ ሲሆን ቡድኑ ላስመዘገበው ደካማ ውጤት ተጠቃሽ የተደረጉት አሰልጣኝ ጳውሎስ ጸጋዬን ለማሰናበት ከውሳኔ ላይ ደርሰዋል፡፡ በምክትሉ በረከት ደሙ ጊዜያዊ አሰልጣኝነት የሚቀጥሉም ይሆናል፡፡ የቀድሞው የአርባምንጭ አማካይ በረከት ከተጫዋችነት ራሱን አግልሎ የቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ የሆነው ዘንድሮ ሲሆን ከወራቶች በኋላ ደግሞ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ መሆን ችሏል፡፡
አሰልጣኝ ጳውሎስ ፀጋዬ ከአለማየሁ አባይነህ ክለቡን መልቀቅ በኃላ ቡድኑን ተረክበው አምና ቡድኑ ለጥቂት ከመውረድ ተርፏል፡፡ ዘንድሮ ቡድኑ የተሻለ የተጫዋች ስብስብ በመያዝ እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ጥሩ አቋም ማሳየት ቢችልም ያለፉት ወራት የወረደ አቋም አሰልጣኙንም ለስንብት ዳርጓቸዋል፡፡