የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዛሬ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሲቀጥል መከላከያ አዲስ አበባ ከተማን 1-0 በማሸነፍ በተከታታይ ሽንፈቶች ምክንያት ከተጋረጠበት የወራጅነት ሰጋት መጠነኛ እፎይታ አግኝቷል፡፡
ቁጥራቸው እጅግ ጥቂት ተመልካቾች በታደሙበት ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል የግብ ሙከራዎች ተስተናግደዋል፡፡ በ3ኛው ደቂቃ የመከላከያ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ከግቡ ቅርብ ርቀት ፍቃዱ አለሙ የሞከረውን ኳስ አቤል ያወጣበት የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር፡፡ በ11ኛው ደቂቃ የተሻ ግዛው ከቀኝ መስመር ሳጥን ጠርዝ የመታውን ኳስ ደረጄ አለሙ ያዳነበት ፣ በ18ኛው ደቂቃ ኃይሌ እሸቱ ከርቀት መትቶ ወደ ውጭ የወጣበት ፣ በ28ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርሮ የሞከረውን አቤል ማሞ በአስደናቂ ብቃት ያወጣበት በመጀመሪያው አጋማሽ ከታዩ የጎል ሙከራዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በ33ኛው ደቂቃ ከሚካኤል ደስታ በጥሩ ሁኔታ የተሻገረውን ኳስ ከቅጣት መልስ ወደ አሰላለፉ የተካተተው ምንይሉ ወንድሙ በጥሩ አጨራረስ መከላከያን 3 ወርቃማ ነጥብ ያስጨበጠች ጎል አስቆጥሯል፡፡ ከጎሉ በኋላም የመከላከያ ተጫዋቾች በዛሬው እለት የተከበረውን የስቅለት በአል በሚያሳይ መልኩ በመስገድ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው አንጻር የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን እምብዛም የግብ ሙከራዎች አልተስተናገዱበትም፡፡ አዲስ አበባ ከተማዎች የጨዋታው ጊዜ እየተገባደደ በሄደ ቁጥር የአቻነቱን ጎል ፍለጋ ተጭነው ቢጫወቱም ግልፅ እድሎች መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በ79ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ኃይሌ እሸቱ በግሩም ሁኔታ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ በሚል መሻሩ በአአ በኩል የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር፡፡
ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ነጥቡን 28 በማድረስ ከወራጅ ቀጠናው በ5 ነጥቦች መራቅ ሲችል አዲስ አበባ ከተማ በ16 ነጥቦች ላይ ረግቶ በፕሪምየር ሊጉ የመቆየት ተስፋው የመሟጠጥ ላይ ይገኛል፡፡