“ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ከሌሎቹ ጨዋታዎች የተለየ ነው” ማርት ኑይ

 

ለአራተኛ ተከታታይ ግዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ለመሆን ተስፋን የሰነቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ የከተማ ባላንታውን ኢትዮጵያ ቡናን ቅዳሜ ይገጥማል፡፡ ፈረሰኞቹ ባሳለፍነው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ መጋራታቸውን ተከትሎ ከተከታዮቻቸው የነበራቸውን የነጥብ ልዩነት ማስፋት የሚችሉበትን እድል አምክነዋል፡፡

ከሶዶ መልስ ለተጫዋቾቻቸው በቂ እረፍት ሰጥተው ጠንካራ ዝግጅት እንዳደረጉ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ማርት ኑይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ “ድቻ በርቀት ተጉዘን ከምንገጥማቸው ክለቦች አንዱ ስለሆነ ከጨዋታ በኃላ ለሁለት ቀናት ለተጫዋቾቼ እረፍት ሰጥቼ ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎ ያደረግነው ዝግጅት በጣም ጥሩ ነው፡፡ 24 ጤነኛ የሆኑ ተጫዋቾች አሉን፡፡ ስለዚህም ለጨዋታ ዝግጁ ነን፡፡”

ሐሙስ በተደረጉ ጨዋታዎች የሊጉ አናት ላይ ከፈረሰኞቹ ጋር የተቀመጡት ደደቢት፣ ሲዳማ ቡና እና በቅርብ ርቀት የሚገኘው አዳማ ከተማ ወሳኝ ነጥቦችን ጥለዋል፡፡ አሰልጣኝ ኖይ ግን የቡድኖችን ነጥብ መጣል ተከትሎ ስለሚፈጠረው ነገር እምብዛም አስተያየት መስጠት አልፈለጉም፡፡ “እኔ የሌሎቹን ነጥብ መጣል አልመለከትም፡፡ እኔ የራሴን ቡድን ነው የምመከተው፡፡ ገና ረጅም ጉዞ ይቀረናል፡፡ ልጆቼን ከፊታችን የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታም ስለሚጠብቅን ጤነኛ እና የነቁ ማድረግ አለብኝ፡፡ ይህ ነው የእኔ ስራ ፡፡ እኛ ይህ ቡድን ነጥብ እየጣለ ነው ሌላኛው ሶስት ተከታታይ ጨዋታ እያሸነፈ ነው እያልን የሂሳብ ስሌት ውስጥ አንገባም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚሰራውን ስራ እናያለን ከዛ በተረፈ የቀረውን ጨዋታ የወዳጅነት ጨዋታ ቢሆንም ለማሸነፍ ጥረት እንደርጋለን፡፡ ካሸነፍን ደስተኛ እንሆናለን፡፡ ከተሸነፍን ደግሞ ተጋጣሚያችን ከእኛ ተሸሎ ከነበረ እና አቻ ብንወጣም ጉዟችንን እንቀጥላለን፡፡ ሁሌም ግን ጥሩ ውጤትን ይዞ መምጣት ነው አላማችን፡፡”

ሆላንዳዊው አሰልጣኝ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ክለቦች አንፃር ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉት ጨዋታ የተለየ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ “እኛ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ ባንክ እና ሌሎቹንም እንጫወታለን፡፡ ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ከሌሎቹ ጨዋታዎች የተለየ ነው፡፡ በድሮው ግዜ እንደነበረው በግላስኮው ሴልቲክ ከሬንጀርስ፣ ሊቨርፑል ከኤቨርተን እንዲሁም ኢንተር ከኤሲ ሚላን ደርቢ ነው ይህም በሁለት የተለያዩ ፅንፍ ያሉ የከተማ ክለቦች የሚያደርጉት የደርቢ ጨዋታ ነው፡፡ እኔ ተስፋ ማድርገው በሁለቱም ክለቦች በኩል ተመልካቹን የሚያዝናና እግርኳስ እንድንመለከት ነው፡፡”

Leave a Reply