“ፍላጎታችን ወደ ዋንጫ ፉክክሩ መቅረብ ነው” ገዛኸኝ ከተማ

 

ባሳለፍነው ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈትን የቀመሰው ኢትዮጵያ ቡና በ23ኛ ሳምንት ከከተማ ተቀናቃኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ይፋለማል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት ባይችልም አዲስ አበባ ላይ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በንፅፅር ማሸነፍ ችሏል፡፡ ቡድኑ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ሊመልሰው የሚችለው ወሳኝ ግጥሚያ የተለየ ዝግጅት አለማድረጉን የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡ “ደርቢው ራሱ አንድ የውድድር አካል ነው፡፡ የውድድር አካል በሆነ ነገር ላይ የተለየ እቅድ አናወጣም፡፡ እኛ በእቅዳችን ነው የምንሄደው፡፡ መርሃ ግብራችን ስለሆነ ከእዛ የተለየ ነገር አንጠብቅም፡፡ ግን እንደውድድርነቱ ታላቅ የሚያደርገው ነገር ሁለቱ ሃያላን ቡድኖች ይገናኛሉ፡፡ በእዚህ በኩል ኢትዮጵያ ቡና በደጋፊዎቹ በኩል ያለውን አመኔታ ለመጠቀም ይፈልጋል፡፡ ይህንን ነው እኛ የምንሰራው እንጂ ከመርሃ ግብራችን ውጪ የምንሰራ ነገር የለንም፡፡”

የወጥነት ችግርን በተለይ በመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያ ሳምንታት ያሳዩት ቡናማዎቹ ተሻሽለው ነጥቦችን ቢሰበስቡም በቅርብ ሳምንታት ላይ መውረድ እና መንሸራተተ ታይቶባቸው፡፡ አሰልጣኝ ገዛኸኝም ለክለቡ የሚሰጠው ግምት ከፍተኛ መሆኑ እንደምክንያትነት አቅርበዋል፡፡ “ልጆቹ ላይ ያለው ነገር ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ውድድሮች ነው እያደረግን ያለነው፡፡ በተለይ ደግሞ ታሳቢ መደረግ ያለበት ውድድሮቹ መሃል ላይ ለእኛ የሚሰጠው ግምት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ በራሱ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ አይተህ ከሆነ የአባይ ግድብ ዋንጫዎችን እስካሁን በብቸኝነት እየተሳተፈ ያለው ቡና ብቻ ነው፡፡ ሌላው በእያንዳንዱ ውድድር ላይ የምንጓዝበት መንገድ ነው ፤ ምክንያቱም ግብ አስቀምጠናል ስለዚህም ወደእዚህ ግብ ለመድረስ ነው ሙከራችን፡፡”

ቡና በጨዋታው ላይ የኤልያስ ማሞ (ጉዳት) እና ጋቶች ፓኖም (ቅጣት) ግልጋሎት አያገኘም፡፡ ሁለቱ የክለቡ ወሳኝ አማካዮች ባለመኖራቸው በጥንካሬው የሚታወቀው የአማካይ ክፍሉ ክፍተት እንዳይፈጠር ያሰጋል፡፡ “እንደቋሚ ተጫዋችነታቸው የተወሰነ ክፍተት ቢኖረውም ያሉት ወጣት ተጫዋች ደግሞ ከዛ የተሻለ ነገር መስራት እንደሚችሉ እናውቃለን፡፡ ምክንያቱም እነሱ (ኤልያስ እና ጋቶች) በሌሉበትም የተወሰኑ ጨዋታዎች ተጫውተን አሸንፈናል፡፡ ጥሩ ጥሩ ጨዋታዎችንም አድርገናል፡፡ ዛሬ እኛ ማውራት የምንፈልገው በቡድኑ ውስጥ ጥሩ ነገር መስራት የሚችሉ ልጆች አሉ፡፡ ስለዚህም እነዚህን ልጆች ተክተን የተሻለ ነገር መስራት እንፈልጋለን፡፡”

ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባለው የእርስ በእርስ ግንኙነት ታሪክ ከፍተኛ በልጫ ቢወሰድበትም ያለፉትን ሶስት የሊግ ጨዋታዎች በፈረሸኞቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ አልተሸነፈም፡፡ ሆኖም አሰልጣኝ ገዛኸኝ ያለፈው ውጤት በጨዋታው ላይ የሚኖረው ሚና የለም ይላሉ፡፡ “ውድድሮች ባለፉ ግዜ እንዳለፉ አድርገን ነው የምናስባቸው፡፡ ቀጣይ ከፊታችን የሚመጡ ውድድሮች ናቸው ትኩረት የሚሰጣቸው፡፡ ስለዚህም እኛ ትኩረት የምናደርገው ስለቀጣይ ጨዋታዎች እንጂ ስላለፈ ታሪክ አይደለም፡፡ በእለቱ የምንሰራው ስራ ላይ ነው ትኩረታችን፡፡

“አይተህው ከሆነ የነጥብ ልዩነታችን ትንሽ ነው፡፡ እኛም ደግሞ ቀጣይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ወደ ዋንጫ ፉክክሩ መቅረብ ነው ፍላጎታችን፡፡ ከፊት ያለውን ጨዋታ እያሸነፍን ከሄድን የት እንደምንደርስ እንውቀዋለን፡፡” ሲሉ ሃሳባቸውን አጠናቅቀዋል፡፡

Leave a Reply