“ካሸነፍን የሊጉን መሪነት የምናሰፋበትን እድል እናመቻቻለን” ሮበርት ኦዶንካራ

 

 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት የ23ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ ይደረጋል፡፡ ስለደርቢው እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ዩጋንዳዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ስለደርቢው

“ከሳምንቱ መጀመሪያ ጀምሮ ያደረግነው ዝግጅት በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ሁሉም ተጫዋቾች በጥሩ መነሳሳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ነው የሚባል አሳሳቢ ጉዳትም የለብንም፡፡ እናውቃለን እነሱ በመጀመሪያው ዙር እንዳሸነፉን ፤ ስለዚህም ያለፈውን ስህተታችንን አርመን በመከላከሉም ሆኖ በማጥቃቱ ጠንካራ ስራ ሰርተናል፡፡ እኔ እንደማስበው ከሆነ በአሁን ጨዋታ በጎ የሆነ ውጤትን ማግኘት አለብን፡፡ ለደጋፊዎቻችንም ሆነ ለእኛ በኢትዮጵያ ቡና ሁለት ግዜ መሸነፍ ስለሚያሳፍር ይህንን ፈፅሞ እንዳይከሰት ጥንቃቄ መውሰድ አለብን፡፡ ካሸነፍን የሊጉን መሪነት የምናሰፋበትን እድል እናመቻቻለን፡፡ እንደቡድን ጥሩ ስራ ሰርተን ጥሩ ውጤት ማግኘት አለብን፡፡”

የመሪ ቡድኖች ነጥብ መጣል

“የሌሎቹ ክለቦች ነጥብ መጣል እኛን ተጠቃሚ ያደርገናል፡፡ ግን እኛም በዛው ልክ ስለእነሱ ማሰብ የለብንም ፤ ያሉብንን ጨዋታዎች በድል መወጣት አለብን፡፡ ሁሌም ያሉብንን ጨዋታዎች ካሸነፍን የሌላው ውጤት መጠበቅ አያስፈልገንም፡፡”

የዩጋንዳ ደርቢ እና የኢትዮጵያ ደርቢ ልዩነት

“ደርቢ ሁሌም ደርቢ ነው በየትኛውም ሊግ ይሁን ሃገር፡፡ በኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ ደርቢዎች መካከል ያለው ትልቁ እና ዋነኛ ልዩነት ደጋፊ ነው፡፡ በዩጋንዳ ሰዎች በደርቢ ወቅት ልክ እንደኢትዮጵያ በብዛት ወደ ስታዲየሞች የመምጣት ነገር አይታይም፡፡ ሌላው ነገር ግን ለምሳሌ የደጋፊዎች መንፈስ፣ ደስታ፣ ሃዘን፣ የተጫዋቾች እንዲሁም የዳኞች ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ ትልቁ ልዩነት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በሸገር ደርቢ ደጋፊዎች ቡድኖቻቸውን ለማበረታታት ወደ ስታዲየም በብዛት ይመጣሉ፡፡”

Leave a Reply