በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው ጨዋታዎች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ 10፡00 አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የሚፋለሙት ሁለቱ ባላንጣዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው የደጋፊ እንደሚታደምበት ይጠበቃል፡፡ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ የልምምድ ስፍራ እና ቃሊቲ አከባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ቡና የልምምድ ስፍራ ኒያላ ሜዳ የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ሳላዲን ሰኢድ እና ናትናኤል ዘለቀን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ አህመድ ረሺድ እና ሳሙኤል ሳኑሚን ከኢትዮጵያ ቡና ስለደርቢው አናግራለች፡፡
“ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነን” ሳላዲን ሰዒድ
የመሪዎቹ ነጥብ መጣል እና ስለጨዋታው
ቆንጆ ነው ሁሌም ከጨዋታ በፊት የምናደርገው ዝግጅት ነው ያደረግነው እና ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነን፡፡ በኳስ የሚከሰተው ነገር አይታወቅም ግን እኛ ሁሌም ቢሆን ከፊታችን ያሉትን ጨዋታዎች እያሸነፍን መሄድን ነው የምናስበው እንጂ የቡድኖች ነጥብ መጣል እንዳለ ሆኖ እኛ እዛ ላይ ትኩረት አናደርግም፡፡ እኛ ሁሌም ከፊታችን ያለው ጨዋታ ለኢንተርናሽናል ጨዋታም ስለሚጠቅመን እያሸነፍን መሄድ ነው ያለብን፡፡
“በጨዋታው ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ አለብን” ሳሙኤል ሳኑሚ
ስለሸገር ደርቢ እና የኢትዮጵያ ቡና ወቅታዊ ሁኔታ
“አንደያችሁት ለጨዋታው በጥሩ መልኩ ተዘጋጅተናል፡፡ የደርቢ ጨዋታ ስለሆነ ቀላል አይሆንም፡፡ ዋናው ቁምነገር በጨዋታው ላይ ትኩረታ ማድረግ እንዲሁም በጨዋታው ጥሩ ብቃት ማሳየት መቻል አለብን፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ሽንፈት አጋጥሞናል፡፡ በዚህም ደስተኛ አይደለም ምክንያም አሽንፈን ቢሆን ኖሮ ከመሪዎቹ ያለንን ልዩነት እናጠብ ነበር፡፡ ቅዳሜ ባለው ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ አለብን፡፡ አንዱ ነገር ሁለቱን የቡድናችንን አማካዮች ጋቶች እና ኤልያስን አጥተናል፡፡ ቢሆንም በእኔ እምነት በአማካይ ስፍራ የሚጫወቱ ሌሎች ጥሩ ተጫዋቾች አሉን፡፡ በቅዳሜ ጨዋታ ጥሩ ውጤት እንደምናስመዘገብ አስባለው፡፡ ቅድም እንደተናገርኩት ዋናው እና ወሳኙ ነገር ቢኖር ትኩረት መስጠታችን ላይ ነው፡፡”
በደርቢው ግብ ስለማስቆጠር
“የቅዱስ ጊዮርጊስን የአጨዋወት ዘይቤ በደንብ እረዳለው፡፡ በመልሶ ማጥቃት መጫወት የሚችል ቡድን እንዳላቸው አውቃለው፡፡ እኔ ስራዬ የሆነው ግብ ለማስቆጠር ነው ወደ ሜዳ የምገባው፡፡ ሌሎች ነገሮች ወደ ጎን ትቼ በጨዋታው ላይ ቡድኔን የሚጠቅም ስራ ለመስራት ነው ሃሳቤ፡፡”
“አላማችን ማሸነፍን ነው” አህመድ ረሺድ
ስለወቅታዊ አቋም
“በጣም በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅተናል፡፡ የአቋም መዋዠቅ በቅርብ ሳምንታት ማሳየታችን በደርቢ ጨዋታ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብዬ አላስብም፡፡ በኳስ ጨዋታ የሚጋጥም ነገር ነው፡፡ ጥሩ ሆነን ነው እየተሸነፍን ያለነው እንጂ ተበልጠን አይደለም፡፡ ይህንን ነገር ደግሞ ከስህተታችን ተምረን የደርቢውን ጨዋታ ለማሸነፍ በሙሉ ዝግጅት ላይ ነው ያለነው፡፡ ምክንያቱም የኳስ ሂደት ስለሆነ ማሸነፍ መሸነፍ አለ፡፡ እኛም ከስህተታችን ተምረን ለጨዋታው ተዘጋጅተናል፡፡”
ስለዋንጫ ፉክክሩ እና የኢትዮጵያ ቡና ተስፋ
“እንደሚታወቀው ከመሪዎቹ ያንያህል በነጥብ አልራቅንም፡፡ ካሸነፍን አንድ ነጥብ ልዩነት ነው የሚኖረን፡፡ ከዋንጫው ፉክክር እንወጣለን ብለን አናስብም፡፡ አላማችን ማሸነፍን ነው፡፡ እናሸንፋለን ግን ብለን ስንገባ ጎላችንን ገልጠን አይደለም አቻ ለእኛም ጥሩ ውጤት ስለሆነ፡፡ ጨዋታው በአሸናፊነት ካጠናቀቅን እኛ ወደ ዋንጫው ፉክክሩ የማንመልስበት ምንም ምክንያት የለም ብዬ አስባለው፡፡”
“ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የምናደርገው ጨዋታ ሁሌም ትልቅ ጨዋታ ነው ” ናትናኤል ዘለቀ
ስለዝግጅት
ከሌላው ግዜ የተለየ ብዙ ዝግጅት አላደረግንም፡፡ ለሁሉም ቡድኖች እንደምንዘጋጀው ጥሩ ትኩረት ሰጥተን ተዘጋጅተናል፡፡ ይህ ጨዋታ ለእኛ ወሳኝ ነው፡፡ ሌሎቹም ቡድኖች በሊጉ ነጥብ ጥለዋል፡፡ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመን መሪነታችን እናጠናክራለን ብለን ነው የምናስበው፡፡
ስለደርቢው
ትልቅ ጨዋታ ነው ሁሌም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የምናደርገው ጨዋታ፡፡ ብዙ ደጋፊዎች እንዳሏቸው የታወቀ ነው፡፡ በእኛም ደጋፊዎች በኩል ተመጣጣኝ የሆነ ድጋፍ ነው የሚታየው፡፡ ብዙም ጫና የለውም ግን መሪዎቹ ተርታ እንደመገኘታችን እነሱም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ አሉ የግድ ነጥባችንን ማራቅ እንፈልጋለን፡፡ ደግሞም የበላይነታችን ማሳየት ስለምንፈልግ የግድ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ አለብን፡፡