የጨዋታ ሪፖርት | የሸገር ደርቢ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ቅዳሜ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሲጠናቀቅ በጉጉት የተጠበቀው የሸገር ደርቢ 10:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ተካሂዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው ተመልካች ከጠዋት ጀምሮ ሰልፍ በመያዝ ወደ ስታድየም የገባ ሲሆን ስታድየሙ በተመልካች የተሞላውም ቀደም ብሎ ነበር፡፡ በዚህም በርካታ ሰዎች ቦታ በማጣት ለመመለስ ተገደዋል፡፡

እንደተለመደው የአአ ስታድየም በሁለት እኩል ቦታ ተከፍሎ በቀኝ የኢትዮጵያ ቡና ፣ በግራ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በመቀመጥ ደማቅ ድጋፍ ያሳየዩ ሲሆን በተለይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በኢትዮጵያ ባልተመደ መልኩ በቀይ እና ቢጫ ፊኛዎች ስታድየሙን አድምቀውታል፡፡

በሳሙኤል ሳኑሚ አማካኝነት የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቀዝቀዝ ብሎ የተጀመረ ሲሆን በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል የተደረጉት የማጥቃት ሙከራዎች ኢላማቸውን ባልጠበቁ ሙከራዎች እና በተደጋጋሚ በሚሰሩ ጥፋቶች በሚቆራረጡ እንቅስቃሴዎች ታጅቦ ቀጥሏል፡፡

በ18ኛው ደቂቃ መስዑድ መሀመድ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ በጊዮርጊስ ተከላካዮች ተገጭቶ ሲወጣ አብዱልከሪም አግኝቶት በቀጥታ ሲሞክር የግቡ ቋሚ መልሶታል፡፡ የተመለሰውን ኳስ በሳጥን ውስጥ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ኢኮ ፌቨር አክርሮ በመምታት ኢትዮጵያ ቡናን ቀዳሚ ያደረገች ጎል አስቆጥሯል። ናይጄሪያዊው የመሀል ተከላካይ በመጀመርያው ዙር በሸገር ደርቢ ላይም የኢትዮጵያ ቡናን የማሸነፍያ ጎል ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና የበላይነት ቢቀጥልም ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር የጨዋታው ፍጥነት እየወረደ እና ግጭቶች እያመዘኑበት መጥቷል፡፡ በዚህም በ38ኛው ደቂቃ ዩጋንዳዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በደረሰበት ጉዳት በዘሪሁን ታደለ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ በአጠቃላይ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተጠናቀቀው የተቀዛቀዘ እና ጥንቃቄ የበዛበት እንቅስቃሴ አሳይቶ ነበር፡፡

በሁለተኛው ግማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳነ ግርማን በአቡበከር ሳኒ ቀይሮ በማስገባት የተጫዋቾችን ሚና በማሸጋሸግ የጀመረ ሲሆን ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ በመስመር በኩል ጥቃት በመሰንዘር ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች በጥልቀት በመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት እድሎችን ለመፍጠሮ ጥረዋል፡፡

በ49ኛው ደቂቃ ፕሪንስ ከቀኝ መስመር ጥሩ ኳስ አሻምቶ ኤኮ ሊያወጣ ሲሞክር ኳስ ወደራሱ ግብ ሄዳ ለጥቂት የወጣችው ኳስ ፣ በ53ኛው ደቂቃ ሳላዲን ከአዳነ የደረሰውን ኳስ አክርሮ ባለመምታቱ ያመከነው እድል ፣ አበባው ቡታቆ በግምት ከ30 ሜትር በግቡ ትይዩ የተሰጠውን ቅጣት ምት በድንቅ ሁኔታ መቶ ሀሪሰን በቅልጥፍና ያዳነበት ፣ በ61ኛው ደቂቃ ሳላዲን ሰኢድ ከመሀል የተሻገረለት ኳስ ከሀሪሰን ጋር ቢያገናኘውም በሀሪሰን አናት ላይ ከፍ አድርጎ ለማስቆጠር ሲሞክር ሀሪሰን በቀላሉ የያዘበት እድሎች ቅዱስ ጊዮርጊስ አቻ ለመሆን የተቃረበባቸው ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ኢትዮጵያ ቡናዎችም ከግብ ክልላቸው ርቀው እየተጫወቱ የነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ከጀርባቸው  ትተውት የሚሄዱትን ቦታ በመጠቀም በተለይ በሳኑሚ አማካኝነት ጥቂት የግብ እድል ለመፍጠር ሙከራዎች አድርገዋል፡፡ በተለይም በ64ኛው ደቂቃ እያሱ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ መስዑድ በግንባሩ ለማስቆጠር ሞክሮ ሳይሳካለት ሲቀር አስቻለው በቮሊ መትቶ ያመከነው ኳስ ተጠቃሽ ነበር፡፡

በ66ኛው ደቂቃ ሳላዲን ሰይድ በኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል ውስጥ በተሰራበት ጥፋት ምክንያት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ መትቶ በማስቆጠር ቅዱስ ጊዮርጊስን አቻ አድርጓል፡፡ ለሳላዲን ይህ ግብ በውድድር አመቱ 16ኛ ጎል ሆና ስትመዘገብ በሊጉ ደግሞ 11ኛ ጎሉ ሆናለች፡፡

ከአቻነት ጎሉ በኋላ በሁለቱም በኩል ከርቀት እና ከቀሙ ኳሶች ከሚገኙ የግብ እድሎች ግቦች ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ ቡና በኩል በአስቻለው ግርማ በ68ኛው ደቂቃ ከርቀት ሞክሮ ኢላማውን የሳተበት ፣ በ73ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻማውን አስቻለው ሞክሮ ዘሪሁን ያዳነበት ሲጠቀሱ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በ71ኛው ደቂቃ ከመሀል የተሻማው ኳስ ኤፍሬምን ሲያመልጠው ሳላዲን አግኝቶ ቢሞክርም ወደውጪ የወጣበት ፣ በ74ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ፕሪንስ ከቅርብ ርቀት አግኝቶ ሞክሮ በግቡ አናት ወደ ውጪ የወጣበት እንዲሁም በ77ኛው ደቂቃ ኒኪማ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ አዳነ በግንባሩ ሞክሮ ሀሪሰን የያዘበት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ ሳሙኤል ሳኑሚ በሳጥን ውስጥ ጥፍት ተሰርቶበታል በሚል ቡናማዎቹ የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄን ቢያቀርቡም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ሆኖም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላም የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች በእለቱ አርቢትሮች ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ባገኙት 1 ነጥብ አማካኝኘት ደረጃቸውን በአንድ ከፍ አድርገዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ40 ነጥቦች (አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከፋሲል ጋር ይቀረዋል) የሊጉን መሪነት ከደደቢት ሲረከብ ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 36 በማድረስ ወደ 4ኛ ከፍ ብሏል፡፡

Leave a Reply