የ2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ወደ ወሳኝ ምዕራፍ ሲሸጋገር በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ የሚገኙት ክለቦች ለቻምፒዮንነቱ የሚያደርጉት ፉክክር ቀልብ ቢስብም በተቃራኒው የመውረድ ስጋት የተጋረጠባቸው ክለቦች በሊጉ ለመቆየት የሚያደርጉት ትግልም በአጓጊነቱ ቀጥሏል። አምና የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ አሸናፊ ሆኖ ፕሪምየር ሊጉን የተቀላቀለው ጅማ አባ ቡና ራሳቸውን ከመውረድ ስጋት ነፃ ማድረግ ካልቻሉ ክለቦች አንዱ ነው።
ጅማ አባ ቡና ከአሠልጣኝ ደረጄ በላይ ጋር ከተለያየ በኋላ በርካታ የፕሪምየር ሊጉ ክለቦችን በማሰልጠን ሰፊ ልምድ ያላቸውን እና ብሔራዊ ቡድኑን በጊዜያዊነት ይዘው የነበሩትን አሠልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ ወደ ክለቡ ያመጣ ሲሆን ከአሠልጣኝ ለውጡም በኋላ በተወሰነ መልኩ መሻሻልን አሳይቷል። አሠልጣኝ ገብረመድህን ከጅማ አባ ቡና ጋር ካደረጓቸው 11 ጨዋታዎች ውስጥ በ3ቱ ሲሸነፉ ከሽንፈቶቹ ውስጥ ሁለቱ በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች የተመዘገቡ ናቸው። ቡድኑ ባደረጋቸው የመጨረሻ 9 ጨዋታዎች 4 ግቦችን ብቻ ማስተናገዱ የተከላካይ ክፍሉን ጥንካሬ በግልፅ የሚያሳይ ቢሆንም ግብ በማስቆጠሩ በኩል ያለው ክፍተት ብዙ ጨዋታዎችን ማሸነፍ እንዳይችል አድርጎታል። ይህም ክለቡ የውድድር ዓመቱን በወራጅ ቀጠናው አካባቢ እንዲያሳልፍ ያስገደደው ሆኗል።
አሠልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ ቡድናቸው በፕሪምየር ሊጉ 23ኛ ሳምንት አዳማ ከተማን አስተናግዶ አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በኋላም የክለቡ በሊጉ እንደሚቆይ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል። አሠልጣኙ ጅማ አባ ቡና ከሊጉ እንዳይወርድ ለማድረግ ግን ከፊታቸው ባሉት ወሳኝ ጨዋታዎች በሙሉ አቅማቸው መጫወት እንደሚኖርባቸው ነው ጨምረው የገለፁት።
“በቀጣይ ያሉት ጨዋታዎች ለኛ እጅግ ወሳኝ ናቸው። እኛ እውነት ለመናገር ከአዳማ ጋር በነበረን ጨዋታም 3 ነጥብ ለመውሰድ ተዘጋጅተን ነበር የመጣነው። ከመጀመሪያው የተደራጀ ቡድን ይዘን መቅረብ ይጠበቅብን ነበር ፤ ግን አልሆነም። በወራጅ ቀጠናው ድንበር ላይ ስለምንገኝ በቀጣይ ያሉ 3 እና 4 ጨዋታዎች ወሳኝነት አላቸው። እንደ ቡድን በየጊዜው የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረግን እና ለውጥ እያሳየን ነው። ያሉን ተጫዋቾች ወጣቶችም ስለሆኑ በቀጣይ ጥሩ ነገር ይሰራሉ ብዬ ስለማምን ከመውረድ እንድናለን ብዬ ነው የማስበው።”
አሠልጣኙ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት የፊታችን ረቡዕ በሻምፒዮንነት ፉክክሩ ንቁ ተሳታፊ የሆነውን ሲዳማ ቡና ከሜዳቸው ውጪ ስለሚገጥሙበት ጨዋታም ተጠይቀው “የሲዳማን ጨዋታ ከወዲሁ ለመገመት ያስቸግራል። እስከ ጨዋታው ዕለት ድረስ እንኳን የተጫዋች ጉዳቶችን ጨምሮ ሌሎች ብዙ ነገሮችም ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ሲዳማ ቡና ጠንካራ እና ለዋንጫ እየተፎካከረ ያለ ቡድን ነው። ከባድ ነው ፤ ጠንካራ ትግል ይጠብቀናል። ግን እኛም በዚያው ልክ ተዘጋጅተን ወደሜዳ እንገባለን።” ሲሉ ከጨዋታው አንድ ነገር ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የፕሪምየር ሊጉ ቀሪ 7 ጨዋታዎች ሻምፒዮኑንና ወደ ከፍተኛ ሊጉ የሚወርዱትን ክለቦች ሲለዩ ጅማ አባ ቡናም ከሜዳው ውጪ ከሲዳማ ቡና፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ወልድያ እና ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም በሜዳው ከወላይታ ድቻ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ይጠብቁታል።