ድሬዳዋ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ በባዶ ስታድየም እንዲያደርግ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቅጣት ተጥሎበታል፡፡
ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡናን ባስተናገደበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች በፈፀሙት ከስፖርታዊ ጨዋነት የራቀ ተግባር ነው ፌዴሬሽኑ ቅጣቱን ያሳለፈው፡፡
በቅጣት ውሳኔው መሰረት ድሬዳዋ ከተማ 75,000 ብር እንዲከፍል ሲወሰንበት በመጪው ሀሙስ ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ካለ ደጋፊ በዝግ ስታድየም እንዲጫወት መወሰኑን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን ኮሚቴ በእለቱ ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደው የኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም የፈፀመው ጥፋት የድሬዳዋ ከነማ ደጋፊዎች የፈጠሩበትን የስነልቦና ጫና ከግምት ውስጥ በከተተ መልኩ አንድ ጨዋታ ሲቀጣ የድሬዳዋ ከተማው የህክምና ባለሙያ አስራት ለገሠ ለፀብ የሚያነሳሳ ድርጊት በመፈፀሙ ምክንያት አራት ጨዋታዎች እንዲታገድና 5,000 ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡