የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅቱን ጀምሯል

የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን የማሊን በፊፋ መታገድ ተከትሎ ጋቦን በግንቦት ወር ለምታስተናግደው የአፍሪካ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በማጣርያው ወቅት የነበሩት አሰልጣኞችን በመያዝ ልምምዱን በአዲስ አበባ ስታድየም ጀምሯል፡፡

በአሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ የሚመራው ከ17 አመት በታች ብሀሄራዊ ቡድናችን በማጣርያው የተጠቀመባቸው ተጫዋቾችን ጨምሮ በዚህ ሳምንት የተደረገው የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ የመለመሏቸው ተጫዋቾችን ያካተቱ ሲሆን ዛሬ ረፋድ ላይ በነበረው የልምምድ ፕሮግራም 4 ግብ ጠባቂዎችን ጨምሮ 36 ተጫዋቾች ተገኝተዋል፡፡ አዳዲስ የተካተቱ ተጫዋቾችም እርስ በእርስ ጨዋታ አድርገው በአሰልጣኞቹ ተለይተዋል፡፡

 

በዚህም በአጠቃላይ በዛሬው ልምምድ ላይ ከተገኙት 36 ተጫዋቾች መካከል 12 ነባር እና 13 አዳዲስ ተጫዋቾች በአጠቃላይ 25 ተጫዋቾች መያዛቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አሰልጣኝ አጥናፉ ባለው አጭር ጊዜ ተጫዋቾችን ቶሎ በመለየትና የኤምአርአይ ምርመራ በማድረግ ለውድድሩ ዝግጅት እንደሚያደርጉ ገልጸው ከጋቦን የአየር ንብረት ጋር የሚቀራረብ ከተማ ላይ ዝግጅት ለማድረግ እንዳሰቡ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

ማሊን ተክታ በምድብ ሁለት ከታንዛኒያ፣ አንጎላ እና ኒጀር ጋር የተደለደለችው ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ግንቦት 7 ከታንዛኒያ ጋር በፖር ዠንቲል ኒጀር እና አንጎላ ጋር በተከታታይ የምትጫወት ይሆናል፡፡

Leave a Reply