” በሚቀጥለው ዓመት ጅማ ከተማን በፕሪምየር ሊጉ ውስጥ እናየዋለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” – አቶ ኢሳያስ ጂራ (የጅማ ከተማ ስራ አስኪያጅ)

18 ጨዋታዎችን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በቀጣዩ ዓመት በፕሪምየር ሊጉ የምንመለከታቸውን 3 ክለቦች ለመለየት በተለይም በምድብ ለ ከፍተኛ ፉክክር እየተደረገ ይገኛል። የከፍተኛ ሊጉን ምድብ ለ የምዕራብ ኢትዮጵያው ጅማ ከተማ በ33 ነጥቦች ይመራል። ጅማ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ናሽናል ሲሜንትን 5-2 በማሸነፍ መሪነቱን ማስፋት የቻለ ሲሆን አምና የምድብ ለ አሸናፊ በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ የገባውን ሌላኛው የጅማ ክለብ ጅማ አባ ቡናን ፈለግ ለመከተል እየሰራ ይገኛል። የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ኢሳያስ ጅራ ስለ ክለቡ ዕቅድ፣ እስካሁን ስለደረገው ጉዞ እና በአጠቃላይ በጅማ ውስጥ ስላለው እግርኳሳዊ እንቅስቃሴ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እንድታነቡ ጋብዘናል።

 

ሶከር ኢትዮጵያ:- ስለ ጅማ ከተማ እግርኳስ ክለብ ከምስረታው ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ያለፈበትን መንገድ አጠር አድርገው ይንገሩን?

 

“የጅማ ከተማ እግርኳስ ክለብ ከተመሰረተ ረጅም አመታትን አስቆጥሯል፤ በ1970ዎቹ ውስጥ ነው የተመሰረተው። ነገር ግን የክለቡ ህልውና ብልጭ ድርግም የሚል እንጂ ዘላቂነት ያለው አልነበረም። በዚህ መልኩ ቆይቶ በ1991 ዓ.ም. ክለቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ብሔራዊ ሊግ መግባት ቢችልም በቀጣዩ ዓመት ተመልሶ ወርዷል። በኋላም በ1998 ሐረር ላይ በተደረገው የክለቦች ሻምፒዮና ተሳትፎ በድጋሚ ወደ ብሔራዊ ሊግ አደገ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ብሔራዊ ሊግ ውስጥ ቆይቶ አምና ከፍተኛ ሊጉ ሲጀመር ተሳታፊ ሆኖ ከምድቡም 4ኛ ሆኖ መጨረስ ችሏል።”

ሶከር ኢትዮጵያ:- ዘንድሮ ጅማ ከተማ በከፍተኛ ሊጉ እስካሁን ያደረገው ጉዞ በምን መልኩ ይገልፁታል?

“ጥሩ ነው። ዘንድሮ ክለባችን ግብ አድርጎ የተነሳው ጥሩ ስራ ሰርቶ ወደ ፕሪምየር ሊጉ መግባትን ነው። ይህንንም ለማሳካት ከክረምት ጀምሮ የተጫዋቾች ምልመላ ተደርጓል። በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ የመጀመሪያውን ዙር 1ኛ ሆነን ማጠናቀቅ ችለናል። ነገርግን ይህ ብዙም የሚያኮራ እና የሚያዝናና፣ የሚያዘናጋ ነገር አይደለም። ፉክክሩ ከባድ፤ የክለቦቹ ነጥብም በጣም ተቀራራቢ ነው። ክለባችን አሁን በ33 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ነው እየመራ ያለው። ከ10 በላይ የሚሆኑ ክለቦች ከ20 ነጥብ በላይ ሰብሰበዋል። ይህንን ውጤት አስጠብቀን በሚቀጥለው ዓመት ጅማ ከተማን በፕሪምየር ሊጉ ውስጥ እናየዋለን ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው።”

ሶከር ኢትዮጵያ:- በውድድር ዓመቱ አጋማሽ ከአሠልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ጋር በመለያየት አሠልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስን ወደ ክለቡ አምጥታችኋል። የአሠልጣኝ ለውጡ በክለቡ ያለውን መንፈስ በመረበሽ በውጤቱ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር አይችልም?

 

“በእርግጥ በውድድር ዓመቱ አጋማሽ ጥሩ እየሰራ ከነበረ አሰልጣኝ ጋር ስትለያይ እንደዚህ አይነት ነገር ሊከሰት የሚችልበት ዕድል አለው። ነገርግን አሰልጣኙ የለቀቀበት አግባብ ከክለቡ ጋር በመጋጨት አልነበረም፤ ከቤተሰቡ ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው የአሰናብቱኝ ጥያቄ ያቀረበው። ክለቡም ይህንን በጥሞና አይቶ በስምምነት ለቅቆታል። ክለቡ አሠልጣኙን ሲለቅም ዝም ብሎ ሳይሆን በክለቡ የሰራውን መልካም ስራ ከግምት ውስጥ በማስገባት እስከ ሰኔ ድረስ ባለው ኮንትራት ከሚቀረው ክፍያ ውስጥ የሁለት ወር ደመወዙን በመክፈል ነው። ሰላማዊ በሆነ መልኩ ነው የተለያየነው፤ በጥል ተለያይተን ቢሆን ኖሮ ክለቡን፣ የተጫዋቾቹን እና የደጋፊዎችን ስሜት ሊጎዳ እና ውጤቱ ላይ ተፅዕኖ ሊያመጣ ይችል ነበር፡፡”

“ወደ ክለባችን ያመጣነው አሰልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስ ሲቪው በጣም ጥሩ ነው። ሁለት ክለቦችን ፕሪምየር ሊግ ማስገባት ችሏል – ኢትዮጵያ ውሀ ስፖርት እና ዳሽን ቢራን። ምናልባት ጅማ ከተማን ወደ ፕሪምየር ሊጉ አስገብቶ ለራሱም ሃትሪክ ይሰራል የሚል ሃሳብ ነው ያለን። ያን ልምድ ወደዚህ ማምጣት ነው የምንፈልገው። እስካሁን በመራቸው ጨዋታዎችም የተመዘገበው ውጤት መልካም የሚባል ነው።”

 

ሶከር ኢትዮጵያ:- የከተማችሁ ክለብ የሆነው ጅማ አባ ቡና አምና የከፍተኛ ሊጉን ምድብ ለ በበላይነት በማጠናቀቅ ፕሪምየር ሊጉን መቀላቀል መቻሉ በጅማ ከተማ እግርኳስ ክለብ ውስጥ የመነሳሳት እና ‘እኛም እንችላለን’ የሚል ስሜት ፈጥሯል?

 

“ምንም ጥያቄ የለውም። እንግዲህ የጅማ አባ ቡና እግርኳስ ክለብ እዚህ ከተማ ውስጥ ከመመስረቱ ጀምሮ በጎ ተፅዕኖ ነበረው። አንደኛ ጅማ አባ ቡና ስሙ ይለያይ እንጂ በጅማ ስም የሚጠራ ነው። የአባ ቡና እግርኳስ ክለብን ወደ ፕሪምየር ሊግ መግባት እንደመልካም አጋጣሚ ይዞ ዘንድሮ ክለባችንን ለማጠናከር ጥረት ተደርጓል። እንደ ስፖርቱ አመራርም እንደ ህዝቡም ሁለት የከተማው ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ ቢኖሩ ደስ ይለናል። በክልሉም በኩል ያለው ስሜት ይኼው ነው። ትልቅ ትኩረት እንዲሰጥ የተደረገበትም መነሻው ይኼ ነው። መልካም ተፅዕኖ ነው ያለው፤ ትልቅ ተነሳሽነት ፈጥሯል ብሎ መውሰድ ይቻላል።”

 

ሶከር ኢትዮጵያ:- ጅማ ከተማ አመራሮች ክለቡን ከሜዳ ውጪ ለማጠናከር ምን ያህል እየሰራችሁ ነው? የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በቀጣዩ ዓመት በፕሪምየር ሊጉ በሚሳተፉ ክለቦች ሙሉ በሙሉ እንደሚተገበር ያስታወቀውን የክለብ ላይሰንሲንግ (Club Licensing) መስፈርቶች ጅማ ከተማ እንዲያሟላ ምን እየተደረገ ነው?

 

“እንደኔ ይህ ነገር የኢትዮጵያ እግርኳስን አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ የሚችል መልካም ጅምር ነው። በጅማ ከተማ አሁን ዋና አላማ አድርገን የተነሳነው ፕሪምየር ሊግ የመግባቱን ነገር ማሳካት ነው። እና ለጊዜው በዚህ ዙርያ ብዙ አልተንቀሳቀስንም። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ግፊት ማድረጉ ግን መልካም ነው። ይህን ይህን ካላሟላህ እኔ በማዘጋጀው ውድድር ላይ አትሳተፍም እስከማለት ቢመጣ በእርግጠኝነት የሀገራችን ክለቦች ወደዚህ ሲስተም እንገባለን የሚል እምነት አለኝ። ግዴታ አንድ ክለብ ተቋም መሆን አለበት። ይህ ነገር በፕሪምየር ሊጉ ለመሳተፍ ግዴታ ቢሆን በእርግጠኝነት በ1 ወር ውስጥ እነዚህ ነገሮች መሟላት ይጀምራሉ። አወዳዳሪው አካልም መርሀግብር አውጥቶ መላክ ብቻ ሳይሆን ይሄን ግፊት ማድረግ መቻል አለበት። አሁን እንደ ጅማ ከተማ ምንም የጀመርነው ነገር ባይኖርም ቀስ በቀስ እነዚህን ነገሮች ወደ ማሟላቱ እንሄዳለን ብዬ አስባለሁ።”

 

ሶከር ኢትዮጵያ:- በአሁኑ ሰዓት ጅማ አባ ቡና በፕሪምየር ሊጉ እየተሳተፈ ሲገኝ ጅማ ከተማ ደግሞ የከፍተኛ ሊጉን ምድብ ለ እየመራ ነው። ይህንን ተከትሎ በጅማ እና አካባቢው እግርኳሱ መነቃቃትን እያሳየ ነው?

 

“ይህንን እናንተም በስታዲየም ተገኝታችሁ አይታችሁታል። በጣም ደስ የሚል ደረጃ ላይ ነው ያለው። ህዝቡ ከሜዳ ርቆ ነበር። ትዝ ይላችሁ እንደሆነ አምና የጅማ አባ ቡና እግርኳስ ክለብ ፕሬዘዳንት ቃለ መጠይቅ ሲደረግላቸው ‘ፕሪምየር ሊግ ከመግባታችን በላይ ያስደሰተን ህዝቡን ወደ ስታዲየም መመለሳችን ነው’ ብለው ነበር። አሁን ያለው ስሜት የሚገርም ነው። ከተማው ውስጥ እግርኳሱ ዋና አጀንዳ ሆኗል። ወጣቶች ትልቅ ተስፋ ሰንቀው ባሉት የማሰልጠኛ ስፍራዎች ላይ ሲገኙ ታያቸዋለህ። አሁን ያለውን ስሜት ለማስቀጠል ከዚህ ጎን ለጎን ከተማ አስተዳደሩ የወጣት ቡድኖችን ማጠናከር አለበት የሚል ሃሳብ አለኝ። በየጊዜው የወጣቶች ውድድሮች ተዘጋጅተው ከነዚህ ላይም ተጫዋቾች ለመመልመል እንዲቻል መሆን ይኖርበታል።”

 

ሶከር ኢትዮጵያ:- በመጨረሻም ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ዕድሉን ልስጥ?

 

“የከተማችን ህዝብ ከክለቡ ጎን ሆኖ ደጋፊውም እንደ 12ኛ ተጫዋች ሆኖ ከዚህ በፊትም ሲያደርግ እንደነበረው ክለቡን እንዲደግፍ አደራ እላለሁ። ክለቡ ውጤት ሲያመጣ ብቻ ሳይሆን አቻ ሲወጣም፣ ሲሸነፍም መደገፍ አለበት። ይህ ክለብ ፕሪምየር ሊግ ገብቶ እንድናይ የሁሉም ባለድርሻ አካላት እገዛ ያስፈልጋል። በሞራል፣ በገንዘብ፣ ሜዳ ላይም ተገኝቶ በመደገፍ ክለባችንን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማስገባት አለብን የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ።”

1 Comment

Leave a Reply