​የጨዋታ ሪፓርት | አዳማ ከተማ አሁንም በሜዳው በጠንካራነቱ ቀጥሏል 

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ተኛ ሳምንት መርሃግብር በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያስተናገደው አዳማ ከተማ 2-0 በማሸነፍ አሁንም የዋንጫ ተፎካካሪ መሆኑን አስመስክሯል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የሚባልን እንቅስቃሴ ማሳየት ችለዋል፡፡ ነገርግን ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከአዳማ በተሻለ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ወደ ግብ መድረስ ችለዋል በተለይም አጥቂያቸው ሙሉዓለም ጥላሁን በሁለት አጋጣሚዎች ማለትም ከአዳማው ግብ ጠባቂ ጃኮብ ፔንዜ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ያመከናት እንዲሁም የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ በጣም የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

በአንጻሩ አዳማ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ከቋሙ ኳሶች በሚገኙ እድሎች እንዲሁም ከተከላካዮች በሚላኩ ረጃጅም ኳሶች ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡

በዚህም አጨዋወት የተገኙትን ሶስት ጥሩ ጥሩ የማግባት አጋጣሚዎች ሚካኤል ጆርጅ ሳይጠቀምባቸው ቀርትዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ የአዳማው አሰልጣኝ የሆኑት ተገኔ ነጋሽ በመጀመሪያው አጋማሽ ደካማ የአጨራረስ ብቃት ያሳየውን አጥቂውን ሚካኤል ጆርጅን አስወጥተው አማካዮን አዲስ ህንጻን በማስገባት የጨዋታውን ሂደት የቀየረ ወሳኝ ቅያሬ አድርገው ነበር ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት፡፡

ከቅያሬው በኃላ አዳማ ከተማዎች ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ ወስደው መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በ56ተኛው ደቂቃ ላይ በቀጥታ ከተከላካዮች የተሻማውን ኳስ የጨዋታው ኮከብ የነበረው ዳዋ ሆቲሳ ሸረፍ አድርጎ ያቀበለውን ኳስ ወጣቱ ቡልቻ ሹራ ከኤሌክትሪክ ተከላካዮች አፈትልኮ በመውጣት የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን ማድረግ ችሏል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ የግቧ ባለቤት የነበረው ቡልቻ ሹራ ባጋጠመው የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ተቀይሮ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል፡፡
በግቧ መቆጠር የተነቃቁ የሚመስሉት አዳማ ከተማዎች ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ይበልጥ ተጭነው መጫወት ችለዋል፡፡

በ72ተኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ዳዋ ሆቲሳ ተቀይሮ ለገባው አዲስ ህንጻ ያቀበለውን ጣጣውን የጨረሰ ኳስ ተጠቅሞ አዲስ ህንጻ በቀላሉ ደገፍ አድርጎ የአዳማን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ከደቂቃዎች በኃላ በእለቱ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ዳዋ ሆቲሳ ሶስተኛ ግብ መሆን የምትችለውን አጋጣሚ የኤሌክትሪክ ተከላካዮችንና ግብ ጠባቂውን አታሎ ካለፈ በኃላ ወደ ግብ የሞከራት ኳስ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ ልትወጣ ችላለች፡፡
በጨዋታው ሶስቱ የአዳማ ከተማ ተስፈኞች የሆኑት ቡልቻ ሹራ ፣ ሱራፌል ዳኛቸውና በረከት ደስታ ያደርጉት የነበው እንቅስቃሴ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች ፈተና ሁነው ውለዋል፡፡

በዛሬው የ2-0 ድል በመታገዝ አዳማ ከተማ በ38 ነጥብ በ4ተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ራሱን ማቆየት ችሏል፡፡

Leave a Reply