የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት 6 ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ተደርጓል፡፡ ይርጋለም ላይ ጅማ አባ ቡናን የገጠመው ሲዳማ ቡና 1-0 በማሸነፍ ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስኪጫወት ድረስ የሊጉን መሪነት ሲረከብ አአ ከተማ ወደ ጎንደር ተጉዞ ድል አስመዝግቧል፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ ባለሜዳዎቹ ሲዳማ ቡናዎች በእንቅስቃሴ እና በርካታ ሙከራዎችን በማድረግ ተሽለው የታዩ ቢሆንም በቢያድግልኝ ኤልያስ የሚመራው የጅማ አባ ቡና የተከላካይ ስፍራን መስበር ሲቸገር ተስተውሏል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ እጅግ ተሻሽለው መቅረብ የቻሉት አባቡናዎች በሲዳማ ቡና ላይ ወስዶ የታየ ሲሆን በተለይ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ አሜ መሀመድን በመሀመድ ናስር ቀይረው በማስገባት በርካታ እድሎችን መፍጠር ችለው ነበር፡፡
ጨዋታው ወደመጠናቀቂያው ሲቃረብ ሲዳማ ቡናዎች የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመቀልበስ ጫና ፈጥረው የተጫወቱ ሲሆን በ87ኛው ደቂቃ ላይ አዲሱ ተስፋዬ በቀጥታ ወደ ግብ የመታት ኳስ በግቡ ቋሚ ስትመለስ ከግቡ ትይዩ የነበረው ፀጋዬ ባልቻ በማስቆጠር ሲዳማ ቡናን ወሳኝ 3 ነጥብ አስጨብጧል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና የሊጉን መሪነት ነገ ከሚጫወተው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲረከብ በአንፃሩ ጅማ አባ ቡና በወላይታ ድቻ ማሸነፍ ምክንያት ወደ ወራጅ ቀጠናው ገብተዋል፡፡
ወደ ጎንደር ያመራው አዲስ አበባ ከተማ ፋሲለ ከተማ ላይ ወሳኝ የ1-0 ድል በማስመዝገብ በሊጉ ለመቆየት የሚያደርገው ጥረት ላይ ነፍስ ዘርቷል፡፡
በጨዋታው እንግዳው አዲስ አበባ ከተማ በኳስ ቁጥጥር የተሻለ የነበረ ሲሆን የፋሲል ከተማ ደጋፊዎችም በአአ ከተማ እንቅስቃሴ ተደንቀው ለቡድኑ ድጋፍ ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡
በ61ኛው ደቂቃ ከመስመር በኩል የተሻገረው ኳስ በፋሲል ተከላካዮች ሲመለስ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ኃይሌ እሸቱ አግኝቶት ወደ ግብነት ቀይሮ አአ ከተማን ለድል አብቅቶታል፡፡
ከግቡ መቆጠር በኋላ ፋሰሲል ከተማ የአቻነት ጎል ፍለጋ ከግብ ክልላቸው ርቀው ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም በጊት ጋት የሚመራው የተከላካይ መስመርን ማስከፈት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ይልቁኑም አአ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት በርካታ ያለቀላቸው የግብ እድሎችን መፍጠር ችለው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
ድሉ አአ ከተማን ከሊጉ ግርጌ ከፍ ባያደርገውም ነጥቡን 19 በማድረስ በሊጉ የመቆየት ጭላንጭል ተስፋውን አለምልሟል፡፡