የጨዋታ ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ወሳኝ ድል ሀዋሳ ከተማ ላይ አስመዝግቧል 

በ24ኛው ሳምንት የኢትየጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሶዶ ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ወላይታ ድቻ 1-0 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው የወጣበትን ድል አስመዝግቧል፡፡

ቶማስ ስምረቱን በጉዳት ሳይዙ የገቡት ወላይታ ድቻዎች በ4-4-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገቡ መላኩ ወልዴ ፣ መሳይ ጳውሎስ እና መሀመድ ሲይላን በጉዳት ያጡት ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው በ4-2-3-1 አሰላለፍ ገብተዋል፡፡ ሶሆሆ ሜንሳህም የተጣለበት የ4 ጨዋታ ቅጣት በመነሳቱ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ ይህን ተከትሎም ሶሆሆ ተገቢ ተጫዋች አይደለም በሚል ክስ በማስያዝ ጨዋታው ተጀምሯል፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ 15 ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማ ኳስ በመቆጣጠር ሲጫወት ባለሜዳወቹ ድቻዎች በበኩላቸው ግብ ለማስቆጠር ረጃጅም ኳሶችን ወደ ግብ በመላክ እና በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ለመግባት ጥረት አድርገዋል፡፡

በ8ኛው ደቂቃ ከማህዘን ምት በዛብህ መለዩ ያሻገራት ኳስ ሙባረክ ሽኩር በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣችበት የድቻ የመጀመሪ ሙከራ ነበረች፡፡ ሀዋሳዎች በአንፃሩ ፍሬው ሰለሞን በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ ጃኮ አራፋት ከግብ ጠባቂው ወንድወሰን ገረመው ጋር ተገናኝቶ ወደ ላይ ያወጣት ኳስ የመጀመርያ ተጠቃሽ ሙከራቸው ነበር፡፡

ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ጨዋታው አሰልቺ መልክ የያዘ ሲሆን በሽኩቻዎች እና ተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጭ በሚሆኑ ተጫዋቾች ምክንያት ሲቆራረጥ ታይቷል፡፡ በዚህም በሁለቱም ቡድኖች በኩል የሚጠቀስ የግብ እድል ሳይፈጠር ቀጥሏል፡፡

የጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ያለ ግብ ሊጠናቀቅ ነው ተብሎ ሲጠበቅ በተጨማሪው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ተሾመ ያሻማውን ኳስ ዳግም በቀለ ወደ ግብነት ቀይሮ የመጀመርያው አጋማሽ በድቻ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ የጨዋታው እንቅስቃሴ እንደመጀመርያው ሁሉ ብዙም ሳቢ ያልነበረ ሲሆን ያልተገቡ አደገኛ አጨዋወቶች እና ደጋፊዎች የሚሰነዝሯቸው አፀያፊ ስድቦች የሁለተኛው አጋማሽ ክስተቶች ነበሩ፡፡ ሀዋሳወች ኳስ ሲይዙ በዲቻ ተጫዋቾች የሚደርስባቸው ተደጋጋሚ ጥፋቶች አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ተጫዋቾቻቸው ከፍተኛ ተቃውሞ በዳኛው ላይ ሲያሳዩ ተስተውሏል ፡፡

በዚሁ የሁለተኛ አጋማሽ ድቻዎች ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል፡፡ በተለይ በ63ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂው ወንደሰን ገረመው በረጅሙ የላካትን ኳስ በዛብህ መለዮ ተቆጣጥሮ ከግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሶሆሆ በአስደናቂ ሁኔታ ያወጣበት የሚጠቀስ ሙከራ ነበር፡፡ በሀዋሳ በኩል ፍሬው ሰለሞን ከማዕዘን ምት ሲያሻማ አዲስ አለም ተስፋዬ በግንባሩ በመግጨት ግብ ጠባቂው ወንደሰን የያዘበት ፤ በ82ኛው ደቂቃ ምስጋናው ወልደዮሀንስ ከመስመር ያሻገራትን ኳስ ጃኮ አረፋት መቶ ወንደሰን ገረመው በግሩም ሁኔታ ያወጣበት አቻ ሊሆኑባቸው የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ነበር፡፡

ሀዋሳ ከተማ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ወደ ድቻ የግብ ክልል በማመዘን ጫና መፍጠር ቢችሉም ግብ ሳየያስቆጥሩ ጨዋታው በወላይታ ድቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ድሉን  ተከትሎ ከ5 ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ወላይታ ድቻ ነጥቡን 26 በማድረስ ከወራጅ ቀጣናው መውጣት ችሏል፡፡

ወላይታ ድቻ ዛሬ ማሸነፉን ተከትሎ ለተጫዋቾቹ በዛሬው እለት ከ10ሺህ – 5ሺህ የማበረታቻ ሽልማት ያበረከተ ሲሆን የወላይታ ዞን አስተዳደር 200 ሺህ ለክለቡ መለገሱም ታውቋል፡፡

Leave a Reply