የጨዋታ ሪፖርት | የግብ ፌሽታ በታየበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋን አሸንፎ ወደ ሊጉ መሪነት ተመልሷል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ወደ ድሬዳዋ ያቀኑት ፈረሰኞቹ ድራማዊ ክሰተቶች በተስተናገዱበት እና 8 ግቦች በተስተናዱበት ማራኪ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን 5-3 በሆነ ውጤት በመርታት ከ24 ሰአታት ቆይታ በኃላ ዳግም ወደ ሊጉ አናት ተመልሰዋል፡፡

ከጨዋታው በፊት በ22ኛው ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግደው 3-1 ባሸነፉበት ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም ላይ ጥቂት በቀኝ ጥላ ፎቅ ይገኙ የነበሩ የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች የሰነዘሩትን አፀያፊ ድርጊት በመቃወም በዛሬው እለት ስታድየም የተገኙት የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች የተለያዩ ባነሮችን በማሰራት በአንድነት ተጫዋቾቹን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ነገርግን የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች ለጋቶች ፓኖም ያዘጋጁትን ስጦታ አንድ በድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ የሆነ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ የተዘጋጀውን ስጦታ ከተረከበ በኃላ በቀኝ ጥላፎቅ አካባቢ ሰብሰብ ብለው ወደተቀመጡት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች አምርቶ ያሳየው እጅግ አስነዋሪ ተግባር በስፍራው የተገኙትን የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎችን ያስቆጣ ተግባር ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ከ500 በላይ ኪሎ ሜትርን አቋርጠው ቡድናቸው ለማበረታታት የተገኙት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በድርጊቱ በማዘን ስታድየሙን ወጥተዋል፡፡ ሆኖም በድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎችና በፀጥታ ሀይሎች ጥረት ጨዋታው ከተጀመረ ከ15 ደቂቃዎች በኃላ ደጋፊዎቹ ወደ ሜዳ ሊመለሱ ችለዋል፡፡

የተለያዩ ስሜቶችን ከጨዋታው መጀመር በፊት ያስተናገደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ባለው የደጋፊዎች ድባብ ታግዞ ተጀምሯል፡፡ ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ካሸነፈው ቡድናቸው ውስጥ አርባምንጭ ላይ በተመለከተው 5ኛ ቢጫ ካርድ ምክንያት መሠለፍ ያልቻለውን ግብ ጠባቂውን ሳሞሶን አሰፋን በቢኒያም ሀብታሙ ብቻ ተክተው በተመሳሳይ የ4-4-2 ቅርፅ ጨዋታውን ሲጀምሩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ከተለያየው ቡድናቸው 5 ያክል ተጨዋቾችን ቀይረው በ4-3-3 ቅርፅ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል፡፡

የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው 15 ደቂቃ የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ መሀል ሜዳ ባደላ መልኩ ፈጠን ያለና ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከድሬዳዋ ከተማ በተሻለ ወደ ጎል በመድረስ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡

በአንጻራዊነት የተሻሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ የመጀመሪያ ግባቸውን በ17ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል፡፡ ሳልሀዲን ሰኢድ ወደ ግብ ሲሞክር የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች ተደርበው የተለመሰውን ኳስ ለወትሮው የማጥቃት እንቅስቃሴን በማገዝ በኩል ደካማ እንደሆኑ ከሚነገርላቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ተከላካዮች አንዱ የሆነው መሀሪ መና በግምት ከ25 ሜትር ላይ ከግቡ ትይዩ ያገኛትን ኳስ አክርሮ በመምታት ማራኪ ግብን አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ቻለ፡፡ ለመሀሪ ግቧ በፈረሰኞቹ ማልያ የመጀመርያው ናት፡፡

በድሬዳዋ ከተማዎች በኩል አጥቂው ሀብታሙ ወልዴ በተናጥል ከሚያደርገው ጥረት በስተቀር ይህ ነው የሚባል እንደ ቡድን ጥሩ መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡ ጫናቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በአንፃሩ  በ33ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር በኩል ሳልሀዲን ሰኢድ ላይ በተሰራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ደጉ ደበበ ሲያሻማ የድሬዳዋ ከተማዎቹ ቢኒያም ሀብታሙና ተስፋዬ ዲባባ ባለመናበባቸው የተገኘችውን ኳስ ከመሀል ሾልኮ የወጣው አዳነ ግርማ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ 2-0 ማሳደግ ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተጨማሪ ግቦችን ሊያገኙባቸው የሚችሉበትን አጋጣሚዎች አዳነ ግርማ ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል፡፡

የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል በጭማሪው ሰአት በጨዋታው ደሞቆ የዋለው ሳልሀዲን ሰኢድ ከግራ መስመር ወደ ቀኝ በአግድሞሽ የድሬዳዋ ተከላካዮችን አልፎ ሰብሮ በመግባት የቡድኑን ሶስተኛ ግብ በግብ ጠባቂ ቢኒያም ስህተት ታግዞ በማስቆጠር በስታድየሙ የተገኙት በርካታ ቁጥር ያላቸው የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎችን ተስፋ አስቆርጦ የመጀመርያው አጋማሽ በፈረሰኞቹ 3-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በመጀመሪያው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች ላስተናገዷቸው ሶስት ግቦች ምክንያት የሆነው ግብ ጠባቂውን ቢኒያም ሀብታሙን በወርቅነህ ዲባባ እንዲሁም ዮሴፍ ዳሙዬን በአመሀ በለጠ በመተካት ነበር ጨዋታውን የጀመሩት፡፡

በነዚህ ቅያሬዎች ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት በ49ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ሳልሀዲን ሰኢድ ከመስመር ሰብሮ በመግባት የድሬዎችን የመንሰራራት ህልም ያጨለመች አራተኛ ግብን ማስቆጠር ችሏል፡፡ ይህችም በእለቱ ድንቅ ለነበረው ሳልሀዲን ሰኢድ በሊጉ ያስቆጠራት አስራ ሶስተኛ ግብ ሆና ተመዝግባለች፡፡

ከዚች ግብ መቆጠር በኃላ ድሬዳዋ ከተማዎች የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በዚህም ይሁን እንደሻው ሞክሮ ለጥቂት የከሸፈበት እንዲሁም ሱራፌል ዳንኤል ከቅጣት ምት በቀጥታ ሞክሮ የግቡ ቋሚ የመለሰበት ኳስ ተጠቃሾች ነበሩ፡፡ በዚህ መልኩ ጨዋታው በቀጠለበት ሆኔታ ላይ በ81ኛው ደቂቃ ላይ ፕሪንስ ሴቨሪን አምስተኛዋን ግብ አስቆጠር በሜዳው የተገኙትን አብዛኛዎቹን የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች ሜዳውን ለቀው እንዲወጡ አስገድዷል፡፡ ይህ ጎል ለፕሪንስ በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ የመጀመርያ ግቡ ሆና ተመዝግባለታለች፡፡

ከዚች ግብ መቆጠር በኃላ ድሬዳዋ ከተማዎች ፍፁም ድንቅ ነበሩ፡፡ በተደጋጋሚ በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስም ጥረት ማድረግ ችለዋል፡፡ በዚህም በ85ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ይስሀቅ አማካኝነት አንድ ግብ ማስቆጠር ችለዋል፡፡

በተቆጠረችው ግብ ይበልጥ የተነቃቁት ድሬዳዋ ከተማዎች 87ኛው እንዲሁም በ92+3ኛው ደቂቃ ላይ በአማካያቸው ይሁን እንደሻው አማካኝነት በተመሳሳይ ከግብ ክልል ውጪ አክርሮ በመምታት ሁለት ግቦችን ቢያስቆጥርም ጨዋታው በፈረሰኞቹ የ5-3 የአሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ ነገርግን ድሬዳዋ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ያደረጉት ድንቅ እንቅስቃሴ ተጨማሪ ጥቂት ደቂቃዎች ቢኖሩ ኖሮ ጨዋታውን መልክ ሊቀይሩ የሚችሉበትን እድል መፍጠር በቻሉ ነበር፡፡

በዚህ ውጤት መሠረት ፈረሰኞቹ ነጥባቸውን ወደ 43 በማሳደግ ለ24 ሰአታት ያክል በሲዳማ ቡና ተነጥቀው የነበረውን መሪነት ማስመለስ ችለዋል፡፡

 

Leave a Reply