የሴቶች ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጠናቋል

 

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በተደረጉ 2 ጨዋታዎች ፍጻሜያቸውን ሲያገኙ አአ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አሸንፈዋል፡፡

ረቡዕ በምድብ ሀ ድሬዳዋ ላይ በተካሄደ አንድ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ከ መከላከያ 1-1 አቻ ተለያይተዋል፡፡ በተመሳሳይ በዚሁ ምድብ ማክሰኞ በተደረጉ ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ አዳማ ከተማ 1-1 ፣ ጥረት ኮርፖሬት ቦሌን 1-0 አሸንፈዋል፡፡

5:00 ላይ በተካሄደው የቦሌ እና ጥረት ጨዋታ የባህርዳሩን ክለብ ብቸኛ ግብ በ31ኛው ደቂቃ ያስቆጠረችው ፋጡማ አሊ ናት፡፡ ጠንካራ ፉክክር ባስተናገደው የኤሌክትሪክ እና አዳማ ጨዋታ ደግሞ ዮዲት መኮንን ለአዳማ ፣ አይናለም ጸጋዬ ለኤሌክትሪክ በ1 ደቂቃ ልዩነት ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡

ሰኞ በተደረጉት ጨዋታዎች ደግሞ አስቀድሞ የምድቡ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው ደደቢት ኢ.ወ.ስ. አካዳሚን 4-1 ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና ከንፋስ ስልክ ላፍቶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በ08:30 ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲን የገጠመው አአ ከተማ 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ቱቱ በላይ በቅጣት ምት ቀይ ለባሾቹን ቀዳሚ ስታደርግ ተራማጅ ተስፋዬ 2ኛውን አክላለች፡፡

10:40 ላይ ቀጥሎ በተካሄደው የአቃቂ ቃሊቲ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ፈረሰኞቹ 1-0 ከመመራት ተነስተው ከእረፍት በኋላ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2-1 አሸንፈዋል፡፡

በምድብ ለ ሌሎች ጨዋታዎች የተደረጉት ማክሰኞ ሲሆን መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልደታን ከመመራት ተነስቶ በእጸገነት ብዙነህ እና ረሂማ ዘርጋ ጎሎች 2-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ተከታዩ ሀዋሳ ከተማ አርባምንጭን አስተናግዶ በነፃነት መና ፣ ትዕግስት ዳዊት ፣ ካሰች ፍስሀ ፣ ስንታየሁ ማቲዎስ እና ቅድስት ዘልዳ ግቦች 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ሲያሸንፍ ሲዳማ ቡና ጌዲኦ ዲላን አስተናግዶ 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡

Leave a Reply