ኡመድ ኡኩሪ ለኢትሃድ አሌሳንድርያ ፈረመ

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ የግብፁን ኢትሃድ አሌሳንድርያ በመጪው ክረምት ይቀላቀላል፡፡ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ስሙ ከተለያዩ የሰሜን አፍሪካ ክለቦች ጋር ሲያያዝ የሰነበተው ኡመድ በመጨረሻም የአሌሳንድሪያ ግዛት ክለብ የሆነውን ኢትሃድ ተቀላቅሏል፡፡

ኡመድ ትላንት (ቅዳሜ) ከኢትሃድ ጋር የ3 አመት ኮንትራት የተፈራረመ ሲሆን ስምምነቱን ተከትሎም ከክለቡ ሊቀ-መንበር መሃመድ ማሻሊ እና ሃላፊዎች ጋር የኢትሃድን ማልያ ይዞ ፎቶ ተነስቷል፡፡ የኡመድ የ3 አመት ኮንትራት ዋጋው 500 ሺህ ዶላር እንደሆነም ተነግሯል፡፡

የእግርኳስ ህይወቱን በመከላከያ እግርኳስ ክለብ የጀመረው ኡመድ በ2001 የውድድር ዘመን ባሳየው አስደናቂ አቋም የብዙዎችን ትኩረት ቢስብም በጦሩ ቤት ቀስ በቀስ ያጋጠመው የአቋም መውረድ ከእይታ እስቀመራቅ አድርሶት ነበር፡፡ በተለይም በ2004 በመከላከያ የነበረው የመጨረሻ የውድድር ዘመኑ ብዙም አስደሳች አልነበረም፡፡

በመከላከያ ካሳለፈው 4 የውድድር ዘመን ቆይታ በኋላ በ2005 ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው የጋምቤላው ተወላጅ ለጥቂት ወራት በቅዱስ ጊዮርጊስ ለመላመድ ቢቸገርም የፈረንጆቹ 2013 ከገባ በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ የአፍሪካ ውድድር መልካም ጉዞ ወሳኝ ግልጋሎትን አበርክቷል፡፡ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ኡመድ ይበልጥ አስደናቂ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በ19 የሊግ እና የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች 15 ግቦች ከመረብ ሲያሳርፍ በሊጉ ከሚፈሩ አጥቂዎች ቀዳሚው መሆን ችሏል፡፡

ኡመድ ከኢትዮጵያው ታላቅ ክለብ ጋር የነበረው የ2 አመት ኮንትራት በመጪው ሰኔ የሚጠናቀቅ በመሆኑና የተጫዋቹ ከኮንትራት ነፃ መሆንን ተከትሎ ቅዱስ ጊርጊስ ከወሳኝ አጥቂው ዝውውር ምንም ገንዘብ አያገኝም፡፡

ኢትሃድ በግብፅ እግርኳስ ውስጥ ከ2ቱ ታላላቅ ክለቦች ጋር የሚወዳደር ስኬት ባያስመዘግብም በደጋፊ ብዛት ከታላለቆቹ አል-አህሊ እና ዛማሌክ ቀጥሎ በርካታ ደጋፊ ያለው ክለብ ነው፡፡ ክለቡ በአሌሳንድሪያ ትልቅ የድጋፍ መሰረት ያለው ሲሆን በግብፅ በፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና እግርኳሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በሚሳተፉ ፅንፈኛ ደጋፊዎቹ ( አልትራሶች ) ይታወቃሉ፡፡ በ1914 የተመሰረተው ኢትሃድ ዘንድሮ የተመሰረተበትን 100ኛ አመት በማክበር ላይ ሲሆን በቅርጫት ኳስ በአረብ ሃገራት ትልቅ ስም ያለው ክለብ ነው፡፡


ያጋሩ