የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ከጋና ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ይረዳው ዘንድ በግንቦት ወር መጨረሻ ከዩጋንዳ አቻው ጋር አዲስ አበባ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል።
ዋልያዎቹ በነሀሴ ወር 2008 ዓ.ም. በሀዋሳ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ሲሼልስን ካስተናገዱበት የ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በኋላ ምንም የወዳጅነትም ሆነ የነጥብ ጨዋታዎችን ያላደረጉ ሲሆን ቡድኑን በጊዜያዊነት ይዘው የነበሩት አሠልጣኝ ገብረመድህን ሃይሌ ከለቀቁ በኋላም ለረጅም ጊዜ ያለ አሠልጣኝ ቆይተው ነበር። የመርሃግብር ለውጥ የማይኖር ከሆነም ከዩጋንዳ ጋር የሚደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ቡድኑ በአዲሱ የዋልያዎቹ አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ የሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ ሲሆን ከ9 ወራት በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን ወደ ዓለምአቀፍ ውድድር የሚመልስ ጨዋታ ይሆናል።
የዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዚህ ሳምንት በካምፓላ ባዘጋጀው እና የኢእፌ ፕሬዘዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ ተካፋይ በነበሩበት የሴካፋ አባል ሃገራት እግርኳስ መሪዎች ስብሰባ ላይ የወዳጅነት ጨዋታውን ለማድረግ ድርድር የተደረገ ሲሆን ቅራኔ ፈጥሮ የነበረው የጨዋታውን ቀን የመወሰን ጉዳይ በስምምነት ተቋጭቶ ጨዋታው ግንቦት 26 በአዲስ አበባ እንዲደረግ ተወስኗል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2019ኙን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሰኔ 2 የጋና አቻውን አክራ ላይ በመግጠም ሲጀምር በሐምሌ ወርም በአፍሪካ ሀገራት እግርኳስ ቻምፒዮና (ቻን) በደርሶ መልስ ከጅቡቲ ጋር ይጫወታል። በሰርቢያዊው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ ሚሉቲን ሰርዲየቪች (ሚቾ) እየተመራ በቅርብ ጊዜያት በአፍሪካ እግርኳስ መልካም ነገር እያሳየ ካለው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለማድረግ የታቀደው ጨዋታም ለዋልያዎቹ ጥሩ አቋም መለኪያ እንደሚሆን ይጠበቃል።